ሐምሌ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በርበሬ፣ ሽሮና ቅመማቅሞች ላይ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን አሐዱ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በተጨማሪም ነዋሪዎቹ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ በቀናት ልዩነት የዋጋ ጭማሪው እየተስተዋለ መሆኑን አንስተዋል። አሐዱም በመሪ እና በሳሪስ የገበያ ማዕከላት ቅኝት አድርጓል።
በዚህም በርበሬ በኪሎ ከ1 ሺሕ እስከ 1 ሺሕ 400 ብር፣ ሽሮ በኪሎ 210 ብር ኮረሪማ በኪሎ 3000 ብር ዋጋ እየተሸጠ መሆኑን መመልከት ችሏል።
የበርበሬ እና ሽሮ በባልትና የተዘጋጀው በርበሬ አንድ ኪሎ 1 ሺሕ 200 ብር እና ሽሮ አንድ ኪሎ እስከ 350 ብር በገበያ ላይ እየተሸጠ ይገኛል።
እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያም ሽንኩርት በኪሎ ከ70 እስከ 80 ብር፣ ቲማቲም በኪሎ ከ40 እስከ 50 ብር እየተሸጠ ይገኛል። የሽንኩርት ዋጋ ከሌሎቹ የጨመረ ሲሆን ቲማቲም እና ድንች በአንፃሩ መቀነሳቸውን አሐዱ መገንዘብ ችሏል፡፡ በተጨማሪም አምስት ሊትር ዘይት ከ1 ሺሕ 550 እስከ 1 ሺሕ 700 ብር አሐዱ በተመለከታቸው አካባቢዎች እየተሸጠ ይገኛል።
አሐዱ በተለይ የዋጋ ጭማሪ የተስተዋለባቸው ምርቶችን በተመለከተ የአዲስ አበባን ንግድ ቢሮን የጠየቀ ሲሆን፤ ንግድ ቢሮው ኢትዮጵያ የምትከተለው ነፃ የንግድ ገበያ በመሆኑ 'በዚህ ዋጋ ሽጡ!' ብሎ ማስገደድ እንደማይቻል ገልጿል።
ሆኖም ግን አንዳንድ ምርቶች አሁን የሚበቅሉበት ወቅት በመሆኑ የዋጋ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አሸናፊ ብርሃኑ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ለዚህም በተለይ ሽንኩርት ላይ እየታየ ያለውን ዋጋ ለማረጋጋት እንደ ሶማሌና አፋር ያሉ ቆላማ አካባቢዎች ላይ ትስስር በመፍጠር የቅዳሜና እሁድ ገበያ ላይ በተሻለ ዋጋ እንዲሸጥ እየተደረገ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ምርቱ በገበያ ላይ እያለ የሚያከማቹ እና እንደሌለ አድረገው የሚናገሩ ነጋዴዎች ላይ ግን እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አክለዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ በበርበሬና ሌሎች ቅመማ ቅመሞች ላይ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ነዋሪዎች ገለጹ
