ጥቅምት 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በምሥራቅ አርሲ ዞን አስተዳደር በጉና፣ በመርቲ፤ በሸርካ እና በሆሎንቆ ዋቢ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ላይ ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች የተፈጸሙትን አሰቃቂ ግድያዎች የቤተክርሲቲያኒቷ ቋሚ ሲኖዶስ አውግዟል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖችን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫውም ጥቅምት 14 ለ15 ቀን 2018 ዓ.ም በጉናና መርቲ ወረዳዎች 17 ክርስቲያኖች፣ ጥቅምት 17 ለ18 ቀን 2018 ዓ.ም. በሸርካ ወረዳ 3 ክርስቲያኖች እንዲሁም ጥቅምት 18 ለ19 ቀን 2018 ዓ.ም. በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ 5 ክርስቲያኖች በድምሩ በጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም. ብቻ 25 ኦርቶዶክሳውያን በድንገት ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን አስታውቋል፡፡

ግድያውም ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ መሆኑን የምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የላከውን ሪፖርት ቋሚ ሲኖዶሱ የተመለከተው በከባድና ጥልቅ የኃዘን ስሜት መሆኑን ገልጿል፡፡
በመሆኑም በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት እንዲህ ዓይነቱ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጸም የቆየው በተደጋጋሚ እንደመሆኑ መጠን እንዲህ ዓይነቱ አስነዋሪ ድርጊት በቅዱሳት መጻሕፍት ሆነ በሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል፡፡
በተጨማሪም በነጻነት የማምለክ ሕገ መንግሥታዊ መብትን የሚጋፋ፣ ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር መንፈሳዊ ዕሴቶቻችንን የሚያጠፋ፣ ክብረ ነክና ሊወገዝ የሚገባው ኢ-ስነምግባራዊ ድርጊት በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በጽኑ አውግዞታል።
በመሆኑም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትም ይህን ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ተግባር በጽኑ በማውገዝና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን በሕይወት የመኖርና የእምነት ነጻነት መብትን እንዲያስከብሩ ጠይቋል፡፡

ቋሚ ሲኖዶስሱ ይህን አስነዋሪ ድርጊት የፈጸሙትን ሕገ ወጥ ግለሰቦች ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪም በቀጣይ እንዲህ ዓይነቱ ሕገ ወጥ ተግባር እንዳይደገም አስፈላጊውን የሕግ ከለላ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ከፍተኛ ኃዘን የገለጸው ቋሚ ሲኖዶሱ፤ ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ተመኝቷል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
 
  
  
  
 