ሕዳር 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የፌደራሊዝም አስተምህሮን ተከትሎ የተቀረጸው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት "የከፋፍለህ ግዛው ሥርዓት ነው" በሚል የሚቀርብበት ተደጋጋሚ ትችት፤ የሀገራዊ አንድነትን ዓላማ በተሳሳተ መንገድ የሚያቀርብ ነው ሲል የሕገ-መንግሥት እና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ገልጿል።

አስተሳሰቡ የፌዴራሊዝም ፍልስፍናን ጠንቅቆ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው ያለው ማዕከሉ፤ "ፌደራሊዝም ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር የአብሮነት እሳቤ ያለው እንጂ፤ የመነጣጠል ዓላማ ያለው አይደለም" ብሏል።

የሕገ-መንግሥት እና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለኢየሱስ ታዬ (ዶ/ር) "ፍፁም የተዋጣለት ሕገ-መንግሥት ያለው አንድም ሀገር የለም" ብለዋል።

Post image

የኢትዮጵያን ሕገ-መንግሥት ማሻሻል ቢያስፈልግ፤ እንዴት እና በምን መንገድ እንደሚሻሻል መለየት እንዲሁም በሕግ አግባብ መከናወን እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተውበታል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ "መገናኛ ብዙኃን የ4ኛ መንግሥትነት ሚናቸውን እና ተደራሽነታቸውን በመጠቀም ትክክለኛውን የፌደራሊዝም ጽንሰ ሐሳብ እና ፍልስፍና በሚገባው ልክ ለሕዝብ አላዳረሱም" ሲሉ ተደምጠዋል።

የብዙኃን መገናኛዎች የማኅበረሰቡን አስተሳሰብ በአዎንታዊ መንገድ የመቅረጽ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስታውሰው፤ የተረጋጋ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲፈጠር እና ሀገራዊ አንድነት እንዲጠናከር ሕገ-መንግሥት፣ ሕገ-መንግሥታዊነት እና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ላይ ያለውን የተሳሳተ እና የተዛባ አመለካከት እንዲጠራ መገናኛ ብዙኃን ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

"የሀገርን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ማስተማር ማለት የፖለቲካ ፓርቲን መደገፍ አይደለም" ሲሉም፤ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኃይለኢየሱስ ታዬ (ዶ/ር) ለአሐዱ ሬዲዮ ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ