የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ በሰንደቅ ዓላማ ላይ ለሚከሰቱ ውዝግቦች "ዋነኛ መነሻ" መሆኑን ምሁራን ገለጹ
የፌደራሊዝምና ሕገ-መንግሥት አስተምህሮ ማዕከል በበኩሉ ሕገ-መንግሥቱም ሆነ ፌደራሊዝም ስርዓቱ የችግሩ መነሻ አለመሆኑን ይገልጻል፡፡
ነገር ግን በአተገባበር ችግር የተነሳ በሰነደቅ ዓላማ ላይ ውዝግቦች አለፍም ሲልም ግጭቶች እንዲነሱ እንዳደረገ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያም ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ ዓርማ የረዥም ዘመን ታሪክ አላቸው። በየነገሥታቱ ዘመን ከመካከል ላይ ያለው ምልክት የተለያየ ቢሆንም፤ ዋናው ክፍል ማለትም አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማትን ከላይ ወደታች ደርድሮ ምልክት እንደሆነ ለበርካታ ዓመታት ዘልቋል።
የአሁኑ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አሁን ባለው ቅርጽ ሥራ ላይ የዋለው በ1880ዎቹ መጨረሻ ላይ እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አንድ ጊዜ መንፈሳዊ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ፖለቲካዊ ትርጓሜ እየታከለበት ከዘመን ወደ ዘመን ተሸጋግሯል።
አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ሰንደቅ ዓላማ ከመጽናቱ በፊት ሦስት እርስ በእርስ ባልተያያዙ ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ቀለማት ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር ይነገራል።
ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአዋጅ ቁጥር 863/2006 መሠረት የዓመቱ 2ኛ ወር ጥቅምት በገባ የመጀመሪያው ሰኞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።
በየዓመቱ በተለያዩ መሪ ቃሎች መነሻነት ተከብሮ ሲውል 18 ዓመታት አስቆጥሯል። የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን፡- ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል።
ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ማለት የሕዝብና የሀገር ክብር፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት ከፍ ማለት ነው። እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማ የሀገርና የሕዝብ ያለፈ ታሪክ፣ ወቅታዊ ገጽታና የወደፊት ዓላማ ነፀብራቅ ነው። ለሀገርና ለሕዝብ የጠለቀ ፍቅር፣ ክብርና ቁርጠኝነት ያለው ዜጋ የተግባር ልዕልና የሚገለጸውም ሰንደቅ ዓላማውን በሰቀለበት ማማ ከፍታ ነው።
ይሁን እንጂ፤ አሁን አሁን ሰንደቅ ዓላማ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የፀብ እና የአለመግባባት መነሻ እየሆነ ከመምጣቱም በላይ ተገቢውን ክብር እያገኘ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ይገለጻል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሰንደቅ ዓላማ እና ብሔራዊ ዓርማ ተገቢውን ክብር መስጠት እንደሚገባ በአዋጅ ቁጥር 654/2001 ይደነግጋል። ድንጋጌው የመንግሥት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በየቀኑ ከጠዋቱ 12፡00 እስከ ምሽቱ 12፡00 ሰንደቅ ዓላማውን እንዲሰቅሉ ግዴታ ይጥላል።
ሰንደቅ ዓላማው ሲሰቀልና ሲወርድም ዜጎች ተገቢውን ክብር የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ቢያሰፍርም፤ ተግባራዊ እንደማይደረጉ መታዘብ ቀላል ነው።
በተለይም የክልል ሰንደቅ ዓላማ ከብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ጎልቶ የሚታይበት ሁኔታ ይስተዋላል።
ይህንን በሚመለከት የታሪክ ምሁሩ አቶ በላይ ስጦታው "አለመግባባቱ የሚነሳው ከሕገ-መንግሥቱ ነው" ይላሉ። ቋንቋ ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝም ለዚህ ችግር መነሻ መሆኑን ያምናሉ።
ሌላው የታሪክ ተመራማሪ አቶ ደረጄ ተክሌ በበኩላቸው የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ በሰንደቅ ዓላማ ላይ ለሚከሰቱ ውዝግቦች "ዋነኛ መነሻ" መሆኑን ያነሳሉ።
በክልል አካባቢዎች የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ እንዳይከበር ከሆነባቸው ጉዳዮች ዋነኛው በፖለቲከኞች ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የመጣ እንደነበር ያስረዳሉ።
የሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ ከፌዴራሉ አባል ክልሎች ሰንደቅ ዓላማ ጋር አብሮ ከመጣ፣ በስተቀኝ በኩል ይሆናል ይላል ሕጉ።
ሁለት ከሆኑ ከፍ ብሎ ከመሀል መሆን አለበት። ሁሉም ከሆኑ ደግሞ የክልሎቹ ሰንደቅ ዓላማዎች በፊደል ቅደም ተከተል ቦታቸውን ይይዛሉ።
ነገር ግን አሁን እየተፈጠሩ ላሉት በሰንደቅ ዓላማ ለሚነሱ ችግሮች "የፌዴራል ሥርዓቱ ችግር ነው ማለት አይቻልም" የሚሉት ደግሞ የፌዴራሊዝም እና ሕገ-መንግሥት አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር) ናቸው።
ሕገ-መንግሥቱም ሆነ የፌዴራል ሥርዓቱ በአተገባበር ላይ ችግር እንዳለባቸው ያነሳሉ። "ይህ ማለት ግን ችግሩ እሱ ነው ማለት አይደለም" ብለዋል።
ይህ የብዙ መስዋዕትነት ተምሳሌት የሆነው ሰንደቅ ዓላማ፣ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማስተካከያ እንዲደረግበት በአጀንዳነት ከተያዙ ጉዳዮች ዋነኛው ነው።
ክልሎች በመዝሙሮቻቸው "በአጥንት እና ደም የተገነባ ክልል" የሚል ሀሳብ ቢያነሱም ከፌዴራል መንግሥት የሚነጥል እንዳልሆነ ኃይለየሱስ (ዶ/ር) ይናገራሉ።
በሰንደቅ ዓላማው ላይ ችግሮችም ካሉ በመወያየት በዋናነትም በምክክር ሂደቱ ሊፈቱ እንደሚገባ ያነሳሉ። በተለይም የክልሎች ሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙሮቻቸው መፈተሽ እንደሚገባቸው ገልጸዋል። የዚህ ችግር ዋነኛ መነሻ "የተሳሳተ 'በዳይ ተበዳይ' ትርክት ነው" ይላሉ።
ሌላው ወደ ፌዴራል ሥርዓቱም ስንገባ በቂ ምክክርና ዝግጅት አለመደረጉ ለሚስተዋሉ ችግሮች ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ። መዝሙሮቻቸውን በተለያየ ትርጉም የመስማት አጋጣሚ እንዳጋጠማቸው ገልጸዋል። አብዛኞቹ ችግር እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ከሰንደቅ ዓላማ በተጨማሪ ብሔራዊ ዓርማ ሕዝቦች የሚኖራቸውን አጠቃላይ ፍልስፍና፣ የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም አቅጣጫ የሚያመለክት ነው።
ከ195 ሰንደቅ ዓላማዎች መካከል የ64 ሀገራት ሃይማኖታዊ ምልክትን እንደ ብሔራዊ ዓርማ አካተዋል። 48 በመቶ የሚሆኑት የክርስትና ሃይማኖት፣ 33 በመቶ ደግሞ የእስልምና ሃይማኖትን የሚወክል ዓርማን ተጠቅመዋል።
ዓርማው ብዝኃነትን በአግባቡና በብቃት በማስተናገድ፣ የግለሰብ ነፃነቶችና መብቶችን በአግባቡ በማክበርና ለቡድን መብቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መገንባት ያለመ ነው።
ይህንን በሚመለከት ሐሳባቸውን የሰጡት የሕግ ባለሙያው አቶ ካሳሁን ሙላት፤ "በኢትዮጵያ ብሔራዊ ዓርማ በሰንደቅ ዓላማው ላይ እንዲቀመጥ በግልፅ በሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጠ ነው" ይላሉ።
በተጨማሪም እነዚህንና መሠል ሕጎች በማይከብሩ አካላት ላይ በአዋጁ አንቀጽ 23 ከንዑስ አንቀጽ 2 እስከ 11 የተከለከሉ ተግባራትን በመተላለፍ ጥፋት የፈፀመ እንደሆነ፣፤እስከ ሦስት ሺሕ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ አብራርተዋል።
ማንኛውም ሰው በአዋጁ አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከተውን በመተላለፍ ጥፋት የፈፀመ እንደሆነ፤ እስከ 5 ሺሕ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም 1 ዓመት ከ6 ወር በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።
በአዋጁ የተመለከተውን ጥፋት የፈፀመው በሕግ የ'ሰውነት መብት' የተሰጠው አካል ከሆነ የገንዘብ ቅጣቱ ከሁለት እጥፍ ያላነሰ ይሆናል።
የሕግ ባለሙያው አቶ ካሳሁን ሙላት "ሰንደቅ ዓላማ ለሀገር የሚሰጥ ክብር በመሆኑ ተገቢው ክብር ሊሰጥ ይገባል" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሰንደቅ ዓላማ የሀገር መወደድ መገለጫ ነው። ሕዝቦች ተስማምተው በሕገ-መንግሥቱ የፀደቀውን ሰንደቅ ዓላማ እስኪቀየር ድረስ ተገቢውን ክብር የመስጠት ግዴታ አለብን ሲሉ ገልጸዋል።
በሕገ-መንግሥቱ፣ በሰንደቅ ዓላማ አዋጁም ሆነ በማንኛውም ሕግ ስለ ሰንደቅ ዓላማ የተደነገጉ ሕጎችን ማክበርና ማስከበር እንደሚገባ ተነስቷል።
በተጨማሪም ሰንደቅ ዓላማችን የልዩነት ሳይሆን የአንድነታችን መገለጫ መሆን እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን፤ የዘንድሮም የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ታስቦ ውሏል።