ጥቅምት 21/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የከተማ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች የቴክኒክ ብልሽት ካላጋጠማቸው ወይም የሚታወቅ ችግር ካላጋጠመ በስተቀር፤ ከ20 ደቂቃ በላይ አገልግሎት ማቋረጥ እንደማይችሉ የአዲስ አበባ ከተማ የአውቶብስ አገልግሎት ድርጅት አስታውቋል።
ይህንን ሕግ የተላለፉ አውቶብስ ሹፌሮች ወይም ትኬት ቆራጮችን ተጠያቂ እንደሚያደርግ ድርጅቱ አስጠንቅቋል።
ይህ አሰራር የተዘረጋው ዜጎች በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት በማጣት እንዳይጉላሉና ረዣዥም ሰልፎች እንዳይፈጠሩ ለመከላከል እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የአውቶብስ አገልግሎት ድርጅት የአገልግሎት ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ከበደ፤ የአውቶብሶችን የትራንስፖርት አገልግሎት ፍሰት፣ ምልልስ እና የጊዜ ቆይታ በቅርበት እየተቆጣጠሩ እንደሚገኙ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
እንደ መስመሩ እና እንደ ሰዓት ሁኔታ የሚለያይ ቢሆንም ከ5 ደቂቃ በላይ በአንድ ቦታ ያለ ምክንያት የሚቆሙ አውቶብሶች ላይ ክትትል እንደሚደረግ ተናግረው፤ በተለይ ከ20 ደቂቃ በላይ ያለ አገልግሎት መቆም እንደማይቻል አጽንኦት ሰጥተውበታል።
አቶ እንዳልካቸው አክለውም፤ "በተሽከርካሪዎቹ ላይ አቅጣጫ አመላካች መቆጣጠሪያ (ጂፒኤስ) በመግጠም የአውቶብሱን የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ምን ያህል የተሳለጠ እንደሆነ እና የምልልስ የጊዜ ቆይታን አስመልክቶ ክትትል ይደረጋል" ብለዋል።
በተጨማሪም በአውቶብሶቹ ውስጥ በተገጠሙ ካሜራዎች አማካኝነት የጊዜ ቆይታውን እና የትራንስፖርት አገልሎት አሰጣጡን በሚመለከት ቁጥጥር እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የከተማ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ አገልግሎትን ከ20 ደቂቃ በላይ ያለ በቂ ምክንያት ማቋረጥ እንደሚያስቀጣ ተገለጸ
አውቶብሶች ላይ በጂፒኤስ ቁጥጥር ይደረጋል ተብሏል
 
  
  
 