ሐምሌ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን በቅርቡ 'የግል ትምህርት ቤቶች የሚያደርጉት የክፍያ ጭማሪ ከ67 በመቶ በላይ መብለጥ የለበትም' ሲል ያወጣው መመሪያ በትምህርት ጥራት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ሲሉ የዘርፉ ባለሞያዎች ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 4ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ በ2018 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ 1 ሺሕ 585 የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1 ሺሕ 227 ያህሉ እስከ 65 በመቶ ብቻ የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ ማድረግ እንደሚችሉ የሚፈቅድ መመሪያ አውጥቷል፡፡

በዚህም መመሪያ መሠረት ቅድመ መደበኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ 45 በመቶ ብቻ ጭማሪ ማድረግ እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን፤ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ 40 በመቶ፣ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ 45 በመቶ እንዲሁም፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ 55 በመቶ የክፍያ ዋጋ መጨመር እንደሚችሉ ተመላክቷል።

አሐዱም በዚህ ጉዳይ ላይ በዘርፉ የሚያሳድረገውን ተጽዕኖ በተመለከተ ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ይህ የተማሪዎች የትምህርት ክፍያ ዋጋ ትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ነው የዘርፉ ባለሞያዎች የጠቆሙት።

የክፍያ ጭማሪው የትምህርት ጥራትን የሕብረተሰቡን የመክፈል ብቻ ሳይሆን የመኖርም አቅም ከግምት ያስገባ መሆን እንዳለበት ለአሐዱ የተናገሩት የዘርፉ ባለሞያው ዶ/ር ኤፍሬም ጌታሁን ናቸው።

አክለውም የግል ተቋማት ከጥራት አንጻር የተሻሉ መሆናቸው አንስተው፤ ነገር ግን የክፍያ ዋጋ መናር ተመራጭነታቸው ላይም ተጽዕኖ እንዳለው ጠቁመዋል።

"ተማሪዎች እና ወላጆችን ከትምህርት ጥራት ይልቅ፤ የክፍያ ቅናሽ ላይ እንዲያተኩሩ ያስገድዳቸዋል" ያሉም ሲሆን፤ ከግል ትምህርት ቤቶች ወደ መንግሥት ተቋማት ለመማር የሚሄዱ የተማሪዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አንስተዋል፡፡

"ጭማሪው ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ ካልሆነ ይህ አካሄድ በወላጆች፣ በትምህርት ቤቶችና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ያሻክረዋል" ያሉት ደግሞ የትምህርት ባለሞያ ዶ/ር አዝመራ ላቾሬ ናቸው።

መንግሥት በበኩሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የትምህርት ተቋማት ደረጃቸውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ለመቆጣጠር ጥረት ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የግል ትምህርት ቤቶች በየወቅቱ ማኅበረሰቡን በሚገባ ሳያወያዩ የትምህርት ክፍያ ይጨምራሉ በሚል ቅሬታ የሚያቀርቡባቸው በርካቶች ናቸው፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ