የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት ያከናወነ ሲሆን፤ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችንና የብድር ስምምነቶችን አፅድቋል፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ከስምምነቶች በተጨማሪም የተለያዩ ሹመቶችንም አፅድቋል፡፡

Post image

ከዚህ በተጨማሪም ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ ያፀደቀ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በሙሉ ድምጽ አፅድቋል፡፡

በተመሳሳይም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የፐብሊክ በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለዘላቂና ንጹህ ኢነርጂ ተደራሽነት ለውጥን ለማፋጠን ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የተደረገውን የ294 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅንም አፅድቋል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የፐብሊክ በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ትራንስፎርሜሽን እና ቀጠናዊ ውህደት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ተጨማሪ የብድር ስምምነትን አፅድቋል፡፡

Post image

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም በ2ኛ አስቸኳይ ስብሰባው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011ን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በአብላጫ ድምጽ ማፅደቁ ይታወሳል፡፡

የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በነባሩ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም በፖለቲካ ፓርቲዎች አስተዳደር፣ በምርጫ እና በምርጫ ሥነ-ምግባር የባለድርሻ አካላት መብትና ግዴታ ሚዛናዊነትን ለመጠበቅ የሚያስችል ድንጋጌዎችን ያካተተ መሆኑ በወቅቱ ተገልጾ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በአዋጁ ላይ ተካቶ የነበረው 'አንድ ፓርቲ በሚወዳደርበት ቦታ 3 ሺሕ የድጋፍ ፊርማ ማከተት አለበት' የሚለው አንቀፅ ሲያጠያይቅ ቆይቷል፡፡

በዛሬው ዕለት ይህ አንቀፅ ጥያቄ ሲነሳበት የቆየ መሆኑን የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ በማስታወስ፤ እንዲታጠፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

Post image

ቦርዱ አዲስ ባሻሻለው የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጁ ላይ 'ፓርቲዎች እጩ አድርገው የሚያቀርቡት አካል 3 ሺሕ ሰው ፊርማ ማሰባሰብ አለበት' የሚል ደንጋጌን አስመልክቶ በርካታ ፓርቲዎች ለአሐዱ ሬዲዮ ቅሬታ ሲያሰሙበት ቆይተዋል፡፡

"ይህ ድንጋጌ ሕጋዊ እውቅና ያለውን አንድ ፓርቲን በአዋጅ ሕጋዊነቱን መጣስ ነው" ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት "ምርጫው ተከናውኖ በምርጫው ምንም ድምፅ ባይገኝ የፈረመው 3 ሺሕ ሰው የት ገበቶ ነው? በሚል የተዓማኒነት ጥያቄ ያስነሳል" ሲሉም ለአሐዱ መናገራቸው ይተወሳል፡፡

ምክር ቤቱም የፓርቲዎችን ቅሬታ ተከትሎ ካለው አጭር ጊዜ አንፃር ይህንን መከወን የማያስችል በመሆኑ፤ እንዲታጠፍ የምክር ቤት አባላቱም ጭምር ጠይቀዋል፡፡

ምክር ቤቱም የኢትዮጵያ ምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ አፅድቋል፡፡

ሌለው በዛሬው ዕለት የፀደቀው ረቂቅ አዋጅ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የፐብሊክ በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለዘላቂና ንጹህ ኢነርጂ ተደራሽነት ለውጥን ለማፋጠን ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የተደረገውን የ294 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት ነው፡፡

ስምምነቱን በተመለከተ የመንግሥት ተጠሪ ተስፋዬ በልጅጌ ዶ/ር) የብድር ስምምነቱን አስፈላጊነት ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት፤ 294 ሚሊየን ዶላሩ ስድስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ31 ዓመታት ውስጥ የሚከፈል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Post image

የስምምነቱ ዋና ዋና ገፅታዎች ከዓለም አቀፍ ልማት ማህበር ተገኘው ገንዘብ ከወለድ ነፃ መሆኑም የመንግሥት ተጠሪው ተናግረዋል፡፡

በቀረበው አዋጅ ላይም የምክር ቤት አባላት ሀሳብ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፤ ብድሩ በሚከፈልበት ጊዜ የራቀ መሆኑንና ለታደሽ ሐይል የተሰጠው ትኩረትን በጥሩ ጎኑን አንስተውበታል፡፡

ተፈጥሮን መሰረት በማድረግ የሚሰራበት አንፃር የተሸለ የብድር ስምምነት በመሆኑ እንዲፀድቅ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ለዘላቂና ንጹህ ኢነርጂ ተደራሽነት ለውጥን ለማፋጠን ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የተደረገውን የ294 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት ውይይት ከተደረገበት በኃላ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የፐብሊክ በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ትራንስፎርሜሽን እና ቀጠናዊ ውህደት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል፤ ተጨማሪ የብድር ስምምነትንም አፅድቋል፡፡

ምክር ቤቱ ካፀደቃቸው ሰምምነቶች በተጨማሪም ሌሎች ሪቂቅ አዋጆችን ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል፡፡

Post image

በኢትዮጵያ መንግሥት እና ቻይና መንግሥት መካከል የተደረገውን የወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር ስምምነት የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅም ለዝርዝር እይታ ለሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

በሁለቱ መንግሥታት መካካል በቤጂንግ የተፈረመውን ስምምነት በዋናነትም በወንጀል መካከል ላይ በጋራ ለመስራት በማሰብ መሆኑን የመንግሥት ተጠሪው ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ማስረጃዎችን፣ መረጃዎችንና የወንጀል ፍሬ የሆኑ ግብዓቶችን የመያዝ የመውረስ እና የማገድ ግዴታን የሚጥል ስምምነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ተጠሪው ያቀረቡት አጠር ያለ ማብራሪያ ላይ፤ የምክር ቤት አባላት አስተያየት እና ጥያቄ አንስተዋል፡፡

የምክር ቤት አባሉም ወንጀል ፈፃሚዎች ከኢትዮጵያ ወደ ቻይና እንዲሁም ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ ሸሽተው ለሚመጡ ከባድ ወንጀለኞች የሚረዳ ስምምነት መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተመሳሳይም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በቻይና መንግሥት መካከል የተደረገውን የፍርደኞችን ማስተላለፍ ስምምነት ረቂቅ አዋጅን ለሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚንስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ ረቂቅ አዋጁ የሁለቱ ሀገራት ፍርደኞች በየሀገራቸው ተዘዋውረው የፍርድ ጊዜያቸውን እንዲጨርሱና ወደ ማህበረሰባቸው ተቀላቅለው አምራች ዜጋ እንዳሆኑ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

ይህ ስምምነት በቻይና ውስጥ በእስር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን እንዲሁም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቻይናውያንን ወደ የሀገራቸው ተዘዋውረው የማረሚያ ጊዜያቸውን እንዲጨርሱ የሚረዳ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ጸገነት መንግስቱ፤ ወደ ኮሚቴያቸው የተመሩ ረቂቅ አዋጆች ላይ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

በተለይም ከቻይና ጋር የተደረጉ እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካ እና ብራዚል ሀገራት ጋር ወንጀልን በጋራ ለመከላከል የተደረጉ ስምምነቶችን በበጎ የሚታይ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ መተላለፊያ ሀገር እንመሆኗ ዓለም አቀፍ ወንጅሎች ፈፀመው የሚልፋው አካላት የሚያዙበት በመሆኑ ይህ ዓይነቱ ስምምነት ከሌሎች ሀገራት ጋርም ሊፈፀም ይገባል ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱ 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት ሲያከናውን የተለያዩ ዘጠኝ የሚሆኑ አዋጆች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ