ሕዳር 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በባህር ዳር ከተማ የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሐኪም በነበሩት ዶ/ር አንዷለም ዳኘ ላይ የግድያ ወንጀል በፈፀመው ተከሳሽ ላይ የ25 ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት መወሰኑን የባሕር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍ/ቤት አስታውቋል።

ከፍተኛ ፍ/ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት ተከሳሽ እሱባለው (ሳሙኤል) ነበረ የተባለው ግለሰብ ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 1፡00 እስከ 2፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስ ባሕርዳር ከተማ ሰባታሚት ቀበሌ ልዩ ስሙ ቆሼ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ የጦር መሳሪያ ይዞ ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ወንጀሉን መፈጸሙ ተነግሯል።

ወንጀል ፈጻሚዎቹ በሰዓቱም ከባሕርዳር ከተማ ወደ ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲሄድ የነበረውን ዶክተር አንዷለም ዳኜን የያዘውን ንብረት ለመውሰድ እንዲመቻቸው በማሰብ፤ ያሽከረክር የነበረውን መኪና እንዲያቆም ሲጠይቁት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ሁለት ጥይት በመተኮስ ዶ/ር አንዷለምን ደረቱን እና ክንዱን በመምታት ግድያውን መፈጸማቸው በችሎቱ ተገልጿል።

በዚህም መሠረት ተከሳሹ እሱባለው (ሳሙኤል) ነበረ በፈጸመው የከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ ወይም በአማራጭ የመግደል ወንጀል ፈጽሟል የሚል የመጀመሪያ ክስ ተከሷል።

በተመሳሳይ ጊዜ እና ቦታ ላይ ወደ ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲሄድ የነበረው ዶ/ር በረከት አማረ ላይ ሁለት ጥይት በመተኮስ የመኪናውን ቦዲ በመምታት ተበዳዩን የሳተው በመሆኑ፤ በፈጸመው ከባድ የሆነ ሰው መግደል ሙከራ ወንጀል የሚል ሁለተኛ ክስ ተከሷል።

Post image

እንዲሁም በሦስተኛ ክስ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23(3) ላይ የተመለከተውን ተላልፎ "ሀሰተኛ የቀበሌ መታወቂያ ሰነዶችን መገልገል ወንጀል ፈጽሟል" በሚል በሰሜን ጎጃም ዞን ፍትሕ መምሪያ ክሶች እንደቀረቡበት ተመላክቷል፡፡

ተከሳሹም የቀረቡበትን ክሶች ክዶ የተከራከረ ቢሆንም፤ ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የባሕርዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዐቃቤ ሕግን ማስረጃዎች በመስማት ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ሰጥቶ የመከላከያ ማስረጃዎችን ከሰማ በኋላ ተከሳሹ የቀረቡበትን ክሶች መካለከል ሳይችል መቅረቱ ተገልጿል።

በመሆኑም በሦስቱም ክሶች የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቶ፣ የቅጣት አስተያየቶችን በመመርመር ተከሳሹ በአጠቃላይ በ25 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ በሙሉ ድምጽ ውሳኔ መስጠቱን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታውቋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ