ጥቅምት 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በመዲናዋ ባለ 15 ወለል የሲኒማ ኮምፕሌክስ በዛሬው ዕለት ሥራ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ "ዛሬ ለኪነጥበብ ቤተሰቦች እና ለከያኒያን ተጨማሪ ብስራት የሆነውን አዲሰ እና እጅግ ዘመናዊ አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ሕንፃ ግንባታ አጠናቅቀን መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል" ብለዋል፡፡

በ24,000 ካ.ሜ ላይ ያረፈው ባለ 15 ወለል "አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ" ባለ አራት ወለል የመኪና ማቆሚያ 592 ሕጻናትንና 887 አዋቂዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው ሁለት የሲኒማ አዳራሾችን በቂ ከሆነ የድምፅ ማስተላለፊያ ሲስተም፣ ዘመናዊ የመብራት ስርጭት፣ የአየር መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን ጋር ያካተተ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም፤ ለቢሮዎች፣ ለእስቱዲዮ፣ ለሥዕል እና አርት ጋለሪ፣ ለቤተመፃሕፍት እና ለተለያዩ ተያያዠ አገልግሎቶች፣ ለካፍቴሪያ፣ ለሱፐርማኬት፣ ለምግብ ቤት፣ ለሱቆች፣ ለውበት ሳሎን፣ ለባንክ አገልግሎት፣ የትኬት መሸጫ ቢሮዎች እና ለጉብኝት አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎችንም ማሟላቱ ተገልጿል።

በተጨማሪም በቅጥር ጊቢው ውስጥ የልጆች መጫወቻ የስፖርት ሜዳ፣ የመኪና ማቆሚያና አረንጓዴ ስፍራዎችን ጨምሮ ለማስታወቂያ የሚሆኑ ስክሪኖች እና ዘመናዊ ሊፍቶች እንዲሁም የፓርኪንግ ቴክኖሎጂዎች ተገጥመውለታል።
የከተማ አስተዳደሩ መስከረም 18 ቀን 2018 በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ዘመናዊ የሕጻናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉ ይታወሳል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ