ጥቅምት 10/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት የክብር ዶ/ር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ ትናንት ጥቅምት 9 ቀን 2018 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

የቀብር ሥነ ስርዓታቸውም በዛሬው ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የሚፈፀም ሲሆን፤ የሰላተል ጀናዛውም ዝሁር ላይ ለረጅም ዓመታት ባስተማሩበት ፒያሳ በሚገኘው የኑር(በኒ) መስጂድ የሚከናወን ይሆናል።

Post image

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ዑመር እድሪስን ሥርአተ ቀብር ለማስፈፀም የተቋቋመው ኮሚቴ ባወጣው መርሃ ግብር መሠረት፤ ዛሬ ከቀኑ 6 ሰዓት ፒያሳ በሚገኘው ኑር መስጂድ ሶላተል ጀናዛ ይሰገዳል።

በማስከተልም ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት የክብር ሽኝት ፕሮግራም ይከናወናል።

በመጨረሻም ከቀኑ 10 ሰዓት ፒያሳ በሚገኘው የኑር(በኒ) መስጂድ ሥርአተ ቀብር እንደሚፈጸም ኮሚቴው አስታውቋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በትናንትናው ዕለት፤ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ፕሬዝደንት የክብር ዶክተር ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ወደ አኼራ መሄድ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ "ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር እድሜ ዘመናቸውን ለአንድነታችን የተጉ፣ የሀገር ዋርካ ባለውለታ ነበሩ" ብለዋል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ፕሬዝደንት የነበሩት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ በዲን እውቀታቸው አንቱ የተሰኙ በመንፈሳዊ አገልግሎታቸውም ላቅ ያለ ደረጃ የነበራቸው ናቸው ያሉት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ እሳቸውን ማጣት እጅግ ከባድ መሆኑን ገልጸዋል።

"ጠቅላይ ምክርቤቱ ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ፣ እስላማዊ ባንኮች እንዲቋቋሙ የሰሩት ታላቅ ሥራ በታሪክ ሲታወስ ይኖራል" ያሉት የክብር ዶክተር ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ የሙስሊሙ አንድነት እንዲጠናከር እድሜ ዘመናቸውን መልፋታቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ላበረከቱት ሁሉ ከፍተኛ ክብር እና እውቅና ይሰጣል ብለዋል።

እሳቸውን ማጣት በእጅጉ ትልቅ ሀዘን ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ ከሙስሊሙ አልፎ በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ውዴታን ለማግኘትም የበቁ ታላቅ ዐሊም እንደነበሩ ገልፀዋል።

ለሀገራችን ሙስሉም የከፈሉት ዋጋ እና ያበረከቱት አስተዋፅኦ መቼም አይዘነጋም ያሉት ፕሬዝደንቱ ፣ መልካም ስራቸውን ሁሉ አሏህ እንዲቀበላቸው ምንዳቸውንም ጀነተል ፊርደውስ እንዲያደርግላቸው አሏህን እንለምናለን፣ በያለንበት ዱዓ እናድርግላቸው ነው ያሉት የክብር ዶክተር ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ።

በተጨማሪም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመረ ኢድሪስ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።

በመልዕክታቸውም፤ "የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በማረፋቸው ኀዘን ተሰምቶኛል።" ብለዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር "በአመራር ዘመናቸው የተለያዩ ወገኖች ወደ አንድነት እንዲመጡ እና የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሕግ ዕውቅና እንዲኖረው ያደረጉትን አስተዋጽዖ ሁሌም እናስታውሰዋለን።" ሲሉም በሀዘን መግለጫቸው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቤተሰቦቻቸው እና ለመላ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች መጽናናትን ተመኝተዋል።

#አሐዱ በተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ይመኛል፡፡

‎#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ