በተለያዩ ወቅቶች በሀገሪቱ ተከስተው በነበሩ ግጭቶች ምክንያት የንግድ እንቅስቃሴው ጫና ውስጥ መግባቱ ይገለጻል
በዋናነት ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ገቢ እንድታጣና የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ እንዲዳከም ማድረጉንም ይነሳል።
ይህንንም ተከትሎ በርካታ አልሚዎች ከነበሩበት ዘርፍ እንዲያፈገፍጉና በሥራቸው የነበሩትን ተቀጣሪዎች ለማሰናበት መገደዳቸውንም መመልከት ያስችላል።
አለመረጋጋት በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አቅራቢዎችን ለኪሳራ ሲዳረግ ተገልጋዮችም በአቅርቦት ችግር ለአላስፈላጊ እንግልት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል።
በትላንትናው ዕለትም የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ከባለኃብቶችና ከንግዱ ዘርፍ ማህበረሰብ ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

ውይይቱ በየጊዜው በሚከሰቱ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችና አለመረጋጋቶች የተነሳ ኢኮኖሚው በሚፈለገው መልኩ አለመንቀሳቀሱን ተከትሎ፤ በተስተዋለው የኢኮኖሚ መዳከም ላይ መፍትሄ ለማበጀት ያለመ ነው።
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት በ1939 ዓ›ም ጀምሮ በራሱ በአዋጅ አትራፊ ያልሆነ ማህበር ሆኖ መቋቋሙ ይገልጻል፡፡
ነገር ግን ተቋሙ አትራፊ ባይሆነም በንግዱ ማህበረሰብ ዙሪዩ የሚነሱ ጥያቄዎች ድምፅ በመሆኑ ለ78 ዓመታት እየሰራ ይገኛል፡፡
በውትወታ ሥራዎች በንግድ ማስተዋወቅ ዘርፍ እና በግልግል ላይ ትኩረቱን በማድረግ እየሰራ የሚገኝ ተቋም መሆኑን፤ የማህበሩ ዋና ፀሐፊ መሠረት ሞላ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

ማህበሩ በሰላም እና የንግድ እንስቃሴ ዙሪያም በትላትናው ዕለት የውይይት መድረክ ያዘጋጀ ሲሆን፤ ግብዓቱን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጭምር ለማስረከብ ማሰቡ ተገልጿል፡፡
ዋና ፀሀፊው በውይይት መድረኩ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር "ሀገራችን ቢዝነሳችንም ሰላም ይፈልጋል" ያሉ ሲሆን፤ መድረኩ ለሰላም ዋጋ ሊሰጠው ይገባል በሚል የተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ በተለያዩ ጊዜያት የንግዱን ዘርፍና ሰላም ጋር በተያያዘ ውይይቶችን ያደረገ ሲሆን፤ በትላትናው ዕለት በተለይም የንግዱን ዘርፉ እየጎዱ ስላሉ የሰላም እጦቶች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ዘርፍ ማህበራት ፕሬዝዳንት ዘሀራ መሀመድ በበኩላቸው "ከጸብ የሚገኘው ኪሳራ ብቻ ነው" ያሉ ሲሆን፤ ወንድም ወንድሙን ገድሎ ጀግና አይባልም ብለዋል፡፡

ዛሬ ሰላም ማግኘት ከሀገርም ሆነ ለንግዱ ዘርፈ ወሳኝ መሆኑን በመግለፅ፤ ሁሉም ለሰላም ሊሰራ ይገባል ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ከተፈለገ፤ በኢትዮጵያ ላይ ያሉ ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶችን መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ማንኛውም ባለሀብት መዋለ ንዋዕይ እንዲያፈስ ለማድረግ ከማሰቡ በፊት፤ የሰላም ሁኔታውን መመለከቱ የማይቀር መሆኑም ይነሳል፡፡
በተለይም ከፍተኛ ገንዘብ እና መዋዕለ ንዋይ የሚያፈሱ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴን እንደሚፈልጉ እሙን ነው፡፡
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ይህንን በተመለከተ ሲገልፁም ተፅዕኖው ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩ ሲሆን፤ ሁሉም የሚጎዳ መሆኑ መታወቅ አለበት ብለዋል፡፡
"የውጭ ኃይሎች ወደ ሀገር ኢንቨሰት ለማድረግ እየመጡ ነው" ያሉ ሲሆን፤ ይህንን ለማስቀጠል ከተፈለገ ሰላም ሚናው ላቅ ያለ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢንቨስትመንትን እና ንግድን የተሻለ ለማድረግ ከተፈለገ የሀገር ውስጥ አለመረጋጋቶችን ማስወገድ ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
አብዛኛው ያለመረጋጋትና የሰላም ችግር ያለው ከአዲስ አበባ ውጪ በመሆኑ፤ በርካታ የውጭ ባለሀብቶች እና ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ለመምጣት ጥርጣሬዎች እንዳሏቸውም ተመላክቷል፡፡

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዘሀራ መሀመድ የንግዱ ማህበረሰብ መንግሥትንና በግጭት ውስጠር ያሉ አካለትን ጭር የማቀራረብ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በአንድ ግዜ የሚስተካከል ነገር አለመኖሩን የገለጹት ፕሬዝዳንቷ፤ የሚጠየቁ ጥያቄዎች በርካታ በመሆናቸው በጊዜ ሂደት ሁሉንም ለማስተካከል ይሰራል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያለፉትን ሰባት ዓመታት በዘረፈ ብዙ የውስጣዊ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እየዳከረች መሆኗ ይታያል፡፡
በኦሮሚያ ክልል አምስት ዓመታት የተሻገረ ግጭት እንዲሁም፤ በአማራ ክልል ሁለት ዓመት ያለፈው ውጊያ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ሌላው ደግሞ ከሦስት ዓመት በፊት በስምምነት የተቋጨው የሰሜን ጦርነት፤ በርካታ ውድመትን በኢኮኖሚው ላይ ማሳደሩ ይገልጻል፡፡
በትላትናው ዕለት በነበረው የውይይት መደረክ ላይም ንግግር ካደረጉት መካከል፤ የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ይገኙበታል፡

ጦርነቶች ከተጠናቀቁም በኃላ ቢሆንም በሕዝብ ላይ የሚያደርሱት ስቃይ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ለዚህም እንደ ማሳያ ጃፓንን ጠቅሰዋል፡፡
ኢንቨስትመንትም ሆነ የንግዱ ዘርፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሰላም መረጋጋት የመጀመሪያው ሲሆን፤ ይህም የኢንቨስተሮችን ዕምነት እንደሚጨምር ይገለጻል፡፡
ሌላው እና ዋናው የንብርት ባለቤትነት መብት መሆኑ የሚገለጽ ሲሆን፤ የሕግ የባላይነት በከፍተኛ ሁኔታ ኢንቨስትመንትን እንደሚፈልግም ይነሳል፡፡
የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤው ዋና ፀሀፊ ቀሲስ ታጋይ በበኩላቸው፤ ሰላም ለንግዱ ማህበረሰብ ብቻም ሳይሆን በሥሩ ተቀጥረው ለሚሰሩ ወጣቶች ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ሰላምና ማረጋጋት በየትኛውም አካባቢ ላለ የንግድ እንቅስቃሴ አስፈላጊ በመሆኑ፤ በመንግሥት ኃላፊነት በመውሰድ ሰላም ለማስከበር መስራት እንደሚኖርበት ተገልጿል፡፡
ማህበሩ ሰላም በሌለበት ኢንቨስትመንት ባለመታሰቡ፤ ሁሉም በግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
 
  
  
 