ጥቅምት 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአስቸጋሪ እና ፈታኝ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንደቆምን ሁሉ፣ በተለይም በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ከኢትዮጵያ አጋሮቻችን የምናገኘውን ተመሳሳይ ድጋፍ እናደንቃለን ሲሉ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ተርክሂን ገለጹ፡፡
አምባሳደሩ ይህንን ያሉት ትላንት ምሽት "የሩሲያ ብሔራዊ አንድነት ቀን"ን አስመልክቶ በተከናወነው መርሃ ግብር ላይ ነው፡፡
ዕለቱን አስመልክቶ አምባሳደሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሩሲያ በአስቸጋሪ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ጎን ስትቆም እንደነበር በማስታወስ ከኢትዮጰያ ለሚገኘው አጋርነትም አድናቆት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ከ300 እና ከ400 ዓመታት በፊት ሩሲያ አሁን የገጠማትን አይነት ሁኔታ ገጥሟት እንደነበር የጠቆሙ ሲሆን፤ "ልክ በዚያን ጊዜ ጸንተን እንደቆምን ሁሉ፣ አሁን ጸንተን እንደምንቆም አምናለሁ" ብለዋል፡፡

ነገር ግን ይህን ለማድረግ ብሔራዊ አንድነት ያስፈልገናል ሲሉ አምባሳደር ኤቭጌኒ ተርክሂን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በሁሉም አስቸጋሪ ጊዜያት የአጋሮቻችንን ድጋፍ በእጅጉ እንፈልጋለን ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በሕዝቦች እና በሀገራት መካከል ያለው ትስስር በተለያዩ መንገዶች የተገነባ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የባህል ትስስር ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ የሳይንስ እና የባህል ማዕከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው የተናገሩት።
ለዚሁ ዓላማ ይረዳ ዘንድም በማዕከሉ የኢትዮጰያ የፈጠራ ባለሙያዎችን የሚወክሉ ሰዓሊያንና ቀራፂያን ሥራዎቻቸውን የሚያሳዩበት አውደ ርእይ በይፋ መከፈቱን ገልጸዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ