መጋቢት 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለክልላዊ የላብራቶሪ ጥራት ፍተሻ ማዕከላት ውስጥ የIT ግብዓት እጥረት ላለባቸው የሚከፋፈል ዋጋቸው 160 ሚሊዮን ብር የሚደርስ የላብራቶሪ ግብዓቶችን በዛሬው ዕለት ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።

እነዚህ የላብራቶሪ ግብዓቶች በበጀት ዓመቱ ከየአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) በተገኘ ድጋፍና hicap-ethiopia ጋር በመተባበር ለሁሉም ክልሎች መከፋፈላቸው ነው የተገለጸው።

Post image



የላብራቶሪ ግብዓቶቹም የጤና ስርዓቱን ያግዛሉ የተባሉ ኮምፒውተር፣ ፕሪንተር፣ እና UPS ግብአቶች መሆናቸውን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሃይሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪም በዓለም ባንክ ፕሮጀክት እየተገነቡ ለሚገኙ ላብራቶሪዎች እና በክልሎች የናሙና ትራንስፖርት አገልግሎት የሚያግዙ የትሪፕል ፓኬጅ ግብዓቶች መሆናቸውን አክለዋል።

የአሜሪካ አለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ለላብራቶሪ ግብዓቶች ያደረገውን ድጋፍ በተመለከተም፤ በአፍሪካ ሀገራት ድጋፋን በይፋ ከማቋረጡ በፊት የተሰጡ እንደነበሩ ተመላክቷል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሩ አብደላ በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ ለአገልግሎት አሰጣጡ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው በመጥቀስ፤ ከዚህ ቀደም ወደ 1 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

በመሆኑም ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ም/ ዋና ዳይሬክተሩ፤ ክልሎች የተሰጣቸውን ግብዓት በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ