ጥር 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ናይጄሪያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ ትኩረቱን የሚያደርግ በአፍሪካ የመጀመሪያውን ዩንቨርስቲ፤ በዋና ከተማዋ ሌጎስ ልትከፍት መሆኑን አስታውቃለች።

ዩኒቨርስቲው ለናይጄሪያ ወጣቶች የተሻሻለ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ስልጠና በመስጥት፤ ሀገሪቷን በቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ላይ የሚመሩ ሰዎችን የማፍራት ዓላማን መያዙ ተነግሯል።

በተጨማሪም ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ገበያ ውስጥ ዋና ተዋናይ በማድረግ፤ አህጉሪቱን የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ዓለም አቀፍ ማዕከል የማድረግ ተስፋ እንደተጣለበት ተመላክቷል፡፡

ዩንቨርስቲው ዊኒ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፤ ስያሜውም በኳታር ከተቋቋመውና ከቻይና፣ ህንድ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት ታላላቅ ምሁራንን እና ፈጠራዎችን በመሳባሰብ ከሚታወቀው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋም የተወሰደ መሆኑ ተነግሯል።

ዩኒቨርሲቲውን በናይጄሪያ ለማቋቋም ጥረቶች የተጀመሩት እ.ኤ.አ በ2016 ሲሆን፤ ጥረቱ ከናይጄሪያ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ኮሚሽን ከፍተኛ ድጋፍ እና ተቀባይነት በማግኘት ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑን የኮኔክቲንግ አፍሪካ ዘገባ አመላክቷል፡፡

በዩንቨርስቲው ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ወጣቶች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ብሎክቼይን፣ ክላውድ ኮምፒውቲንግ እና ማሽን ለርኒንግ የትምህርት መስኮች ትምህርት የሚሰጣቸው ሲሆን፤ በፍጥነት በሚለዋወጠው የዓለም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ገበያ ውስጥ መሪ የሚሆኑበትን ክህሎት እንደሚያገኙም ተመላክቷል።

በዚህም የዩንቨርስቲው መከፈት ሥራ አጥነትን ለመቀነስ እና በአፍሪካ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ እውቀትን የታጠቀ ማህበረሰብን ለማፍራት አስተዋጽኦው ጉልህ እንደሚሆን ግምት ተሰጥቶታል፡፡

በዳግም ተገኝ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ