ሰኔ 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ ያቀረበውና 'ዜጎችን ወደ ውጪ ሀገር ለሥራ ስምሪት የሚልኩ ኤጀንሲዎች እስከ 35 ሚሊዮን ብር የሚደርስ የዋስትና ማስያዣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አካውንት ማስቀመጥ አለባቸው' የሚለው አዋጅ፤ "እኛን ከሥራ ውጭ የሚያደርግ ነው" ሲሉ የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ኤጀንሲዎች ቅሬታቸውን ለአሐዱ አቅርበዋል።

‎በኤጀንሲዎቹ ዙሪያ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከ50 ሺሕ ዶላር እስከ 250 ሺሕ ዶላር ለዋስትና ማስያዣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አካውንት ማስቀመጥን የሚያስገድድ ሲሆን፤ "ይህም ድንጋጌ ከተለመደው አሰራር ውጭ ነው" ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡

"ከዚህ በፊት 100 ሺሕ ዶላር ብቻ ለዋስትና ማስያዣ በባንክ ተቀማጭ እንድናደርግ እንጠየቅ ነበር፤ አሁን የቀረበው ግን እኛን አቅም በማሳጣት ሙሉ ለሙሉ ከሥራ ውጭ ሊያደርገን የሚችል በመሆኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ትኩረት ሰጥቶ ይመልከትልን" ብለዋል።

አክለውም፤ "ሚኒስቴሩ ረቂቅ አዋጁን ያዘጋጀው እኛንም ሆነ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በደንብ ሳያወያይና ምክረ ሀሳባችን ሳይቀበል ነው" ብለዋል።
‌‎
‎አሐዱም ይህንን ጉዳይ በመያዝ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን "አዋጁን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከማቅረቡ በፊት አጀንሲዎችን ስለጉዳዩ አላወያየም ነበር ወይ? የኤጀንሲዎቹን ቅሬታንስ እንዴት ይመለከተዋል?" ሲል ጠይቋል።

‎በዚህም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት መሪ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ኤርሚያስ በድሉ በሰጡት ምላሽ፣ "አዋጁ 250 ሺሕ ዶላር እንዲከፍሉ የሚያስገድድ አይደለም" ብለዋል፡፡

‎አዋጁ በአምስት ደረጃ ተከፍሎ ከ50 ሺሕ ዶላር ጀምሮ በ100 ሺሕ፣ በ150 ሺሕ፣ በ200 ሺሕ እና በ250 ሺሕ ዶላር አማራጮች እንዲቀመጥ መደረጉን መሪ ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

"ተቀማጭ የሚደረገው ይህ ገንዘብ፤ ዜጎች አደጋ ሲደርስባቸው ኤጀንሲዎች ቶሎ ምላሽ ካልሰጡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አፋጣኝ ኢንሹራሽ እንዲሰጥ የሚያደርግ አሰራር ነው" በማለትም አብራርተዋል።

‎ኤጀንሲዎች አሁን አስይዘው እየሰሩበት ያለው የገንዘብ መጠን ለሁሉም 100 ሺሕ ዶላር ሲሆን፤ አሁን ግን ደረጃው ዝቅ ብሎ ከ50 ሺሕ ዶላር ጀምሮ መሆኑን ኤርሚያስ አክለዋል።

‎አዋጁ የዋስትና ማስያዣው ገንዘብ ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሂሳብ ቁጥር እንዲገባ የሚያደርገው፤ በኤጀንሲዎች እና በባንኮች መካከል ያለው አሰራር ግልፅ ባለመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

"‎እነዚህ አምስት ደረጃዎች ሲወጡ ጥናት ተደርጎባቸው በመሆኑ 'ኤጀንሲዎችን ይጎዳል' ተብሎ አይጠበቅም" ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ ሚኒስቴሩ ረቂቅ አዋጁን ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመምራቱ በፊት ከውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ኤጀንሲዎች እና ከክልል ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጋር የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ በማዘጋጀት መወያየቱንም ተናግረዋል።

"ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የዜጎችን ተጠቃሚነት ብቻ ሳይሆን፤ ደህንነቱ የተጠበቀ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት እንዲኖር እየሰራ ነው" ሲሉም ለአሐዱ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ