ሰኔ 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በአንዳንድ ወፍጮ ቤቶች እና የንግድ ቦታዎች ላይ የተበላሸ ዱቄትና በርበሬ እየተሸጠ በመሆኑ ማህበረሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚባው የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በባለስልጣኑ የቁጥጥር ዘርፍ ባለሙያ አቶ ሞላ ታደለ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ለጤና ከፍተኛ ችግር የሚያስከትሉ ዱቄትና በርበሬ በአንዳንድ ወፍጮ ቤቶች እና ንግድ ቦታዎች ላይ ሲሸጡ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በዚህ ዓመት ማለትም በ10 ወራት ውስጥ ብቻ ግምቱ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚሆን 257 ኩንታል የተበላሸ በርበሬ ሲሸጥ፤ በማህበረሰቡ ጥቆማ በመያዙ እንዲወገድ መደረጉን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የጤና ችግር የሚያስከትል ከ37 ኩንታል በላይ የሚሆን ዱቄት በተደረገ ክትትል መያዙንም አብራርተዋል።
በተለይም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ በልደታ ክ/ማ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ እና በጉለሌ ክፍለ ከተማ አካባቢ መሰል ምርቶች የተገኙ መሆኑን ባለሙያው ገልጸዋል።
ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ማህበረሰቡን ለጤና ችግር የሚያጋልጡ ማለትም የተበላሸ ዱቄትና በርበሬ በወፍጮ ቤት ውስጥ 'ንጹህ ነው' በማለት እንደሚሸጥ ተገልጿል።
በእንደዚህ አይነት ሕገ-ወጥ ተግባር ተስማርተው የተገኙ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አንስተው፤ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ነጋዴዎችን አስተዳደራዊ እርምጃ እና የብቃት ማረጋገጫ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ መደረጉን ተናግረዋል።
አክለውም በስኳር፣ ዘይት እና ጨው ላይም መሰል ችግር የተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ይህንን ሕገ-ወጥ ድርጊት ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ አለበት ብለዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ለጤና ችግር የሚያጋልጥ የተበላሸ በርበሬ እና ዱቄት በወፍጮ ቤቶች እየተሸጠ በመሆኑ ማህበረሰቡ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ተባለ
