ጥር 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኮሪደር ልማት እና በወንዝ ዳር ልማት በሚፈርሱ ነባር የመኖሪያ መንደሮች የነበሩ እንዲሁም፤ የጋራ የመኖሪያ ቤት ደርሷቸው አካባቢያቸውን በሚለቁ ሰዎች ያደጉ ውሾች በባለቤቶቻቸው በመተዋቸው ባለቤት የሌላቸው የጎዳና ውሾች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ባለቤቶቻቸው ወደ አዲሱ መኖሪያቸው ይዘዋቸው የማይሄዱ ውሾች ለእብድ ውሻ በሽታ መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽፆ እንዳላቸው ለአሐዱ የተናሩት በሚኒስቴሩ ብሔራዊ የዉሻ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪ ዶ/ር ወንዱ መንገሻ ናቸው።

በከተማዋ ውስጥ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚገኘው ባለቤት የሌላቸው ውሾች ከበሽታ ስርጭት በተጨማሪ የከተማዋን ውበትም እየቀነሱ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን ባለቤት የሌላቸውን ውሾች በጊዜያዊነት የማሰባሰብ እና የማከም፣ ባለቤት የማፈላለግ፣ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመስጠት ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስተባባሪው ዶ/ር ወንዱ ተናግረዋል።

የውሻ እብደት በሽታን መቆጣጠር የሚቻለው በማስከተብ ብቻ ሳይሆን የውሻችን ቁጥር በመቆጣጠር እንደሆነም አስተባባሪው ነግረውናል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከ350 ሺሕ በላይ ውሾች እንዳሉና ከእነዚህ ውስጥ 40 በመቶው ባለቤት አልባ መሆናቸውን የተገለጸ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ በዓመት ከ3 ሺሕ በላይ ሰዎች በእብድ ዉሻ ንክሻ ምክንያት ሕይወታቸዉ እንደሚያጡ ተነግሯል፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2030 በሀገር አቀፍ ደረጃ አንድም ሰው በውሻ እብደት በሽታ እንዳይሞት፤ “zero Rabies 2030'' ብሔራዊ የውሻ እብደት በሽታ ማጥፋትና መቆጣጠር እስትራቴጂ አውጥታ እየተገበረች እንደምትገኝ ይታወቃል።