ጥቅምት 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ትግበራ ላይ አዲሱ የተሸከርካዎች ሰሌዳ አስተዋጽኦ እንዳለው የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ለአሐዱ ገልጿል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ ነባሩን የተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ ቁጥር በአዲስ ለመተካት የሚያስችል አዲስ የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሰሌዳ አይነቶችና ምልክቶች መወሰኛና የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 1050/2017 ማውጣቱ ይታወሳል።
አሐዱም "ይህ አዲሱ የተሸከርካዎች መለያ ሰሌዳ ቁጥር በአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ላይ በትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን አስተዋጽኦ እንዴት ይታያል?" ሲል ሚኒስቴር መሰሪያ ቤቱን ጠይቋል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሚንስትር ዴኤታ በረሆ ሀሰን በምላሻቸውም፤ በአዲሱ ሰሌዳ አማካኝነት በነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ጋር በተያያዘ ተሸከርካሪዎች ወደ ሌሎች ሀገራት በነፃነት ገብተው እንዲወጡ እንደሚያደርጋቸው ጠቁመዋል።
አዲሱ የተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ የዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እንዲሁም የስምምነቱን መመሪያ ያሟላ እንደሆነ የገለጹት ሚንስትር ዴኤታው፤ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ እንደሆነም ተናግረዋል።
ይህም በነፃ ንግድ ቀጣናው ስምምነት ላይ ከተሽከርካሪዎች ደህነት ጋር በተያያዘ አጋዥ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በተያያዘ፣ በ2018 ዓም ሙሉ በሙሉ ተሽከርካሪዎችን በአዲስ ታርጋ የመቀየር ሥራ እንደሚሰራ የትራንስፖርት ተናግረዋል።
በአገልግሎት ላይ ያለውን ነባሩን የተሽከርካሪ መለያ ስሌዳ ቁጥር በአዲስ ለመተካት ካስፈለገበት ምክንያቶች ውስጥ፤ ቀደም ሲል የነበረው የተሽከርካሪ መለያ ቁጥር ስሌዳ አመራረትና አሰረጫጨት የአሰራር ክፍተት እና የሃብት ብክነት ሲስተዋልበት የቆየ በመሆኑ ያንን ለመቅረፍ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ነው ሲሉ አስታውሰዋል።
ነባሩ ታርጋ በአዲስ በሚቀየርበት ወቅት የሰሌዳ ማስቀየር ሥራው የሚጠይቀውን ሁሉንም ወጪ የመኪናው ባለንብረት ይሸፍናል ብለዋል።
"ከእዚህ ቀደም የነበረው ታርጋ 9 ሚሊየን መኪኖችን ብቻ መዝግቦ የሚያበቃ ውስን ታርጋ ነበር እስካሁን ባለው መረጃም 1 ነጥብ 6 ሚሊየን የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ተመዝግበዋል፤ የአሁኑ ታርጋ ግን 121 ሚሊየን ታርጋዎችን መመዝገብ ያስችልናል ሲሉም አክለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ አዲሱ ታርጋ ቅየራ የሚከናወንበት ጊዜ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ መሰራት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች መሰራት ስላለባቸው አዲሱ ታርጋ ቅየራ አለመጀመሩን እና ከሁለት ወር ባጠረ ጊዜ አዲሱን ታርጋ መቀየር እንደሚጀመር በተያዘው 2018 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ አዲሱን ታርጋ እንደሚቀየር መግለፁ የሚታወስ ነው።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በአፍሪካ ነፃ ንግድ ትግበራ ላይ አዲሱ የተሸከርካሪዎች ሰሌዳ አስተዋጽኦ እንዳለው የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ገለጸ
