የካቲት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለ6ኛ ጊዜ ያዘጋጀው "የጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ ትውውቅና ትስስር" መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በዩንቨርስቲው አከናውኗል።
በዚህም መርሃ ግብር ላይ የዩንቨርስቲው ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር)፣ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ም/ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኜው፣ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፣ የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የጎንደር ዩኒቨርስቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ደብሬ የኋላ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የዩንቨርስቲው አዲስ እና ነባር ተማሪዎች፣ የከተማዋ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የ"ጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት" በሚል ስያሜ ከ2012 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ፕሮግራም፤ በየዓመቱ ከተለያዩ የሀገሪቱን ክፍሎች ወደ ዩኒቨርስቲው የሚመደቡ ተማሪዎችን በመቀበል፤ ከጎንደር ከተማ ማኅበረሰብና ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የቃል ኪዳን ቤተሰብ በመምረጥና በማስተዋቅ የማስተሳሰር አላማን ያነገበ መርሃ ግብር ነው፡፡
በዛሬው ዕለት ለስደስተኛ ጊዜ የሚከናወነው የትውውቅና ትስስር መርሃ ግብርም፤ የዩኒቨርሲቲው 70ኛ ዓመት እና የስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ 100ኛ ዓመትን በማክበር ላይ በሚገኝበት ወቅት የሚከናወን በመሆኑ አከባበሩን ልዩ እንደሚያደርገው የዩንቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን በመድረኩ ገልጸዋል፡፡

"አዲስ ገቢ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የማስተሳሰር ተግባር በተለያዩ የዓለም ሀገራት በሚኖሩ የትምህርት ተቋማት እንዳለ እንገነዘባለን" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤."የተቀባይ የቤተሰብ ፕሮግራም በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውሮፓና ጃፓን የትምህርት ተቋማት የተለመደ አሰራር እንደሆነ ጥናቶች እንደሚያመላክቱ አስረድተዋልዋል፡፡
ይህንንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ልምድ በመውሰድ ከሀገር ውስጥ ደግሞ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የአብነት ተማሪ ቤት እና ከእስልምና ሃይማኖት የደረሳ ተማሪዎች ትውፊት ላይ በማጣመር፤ ዩዩንቨርስቲው በግንባር ቀደምትነት ይህን የተማሪና ማህበረሰብ ትስስር በማስተዋወቅ ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት እስከአሁን ድረስ ከ3000 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን በቃል ኪዳን ከማኅበረሰቡ ጋር መተሳሰራቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ በርካታ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቅቀው በዩንቨርስቲው መመረቃቸውን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የትውውቅና ትስስር መርሃ ግብሩ ተማሪዎች በጎንደር ቆይታቸው የእንግዳነት ስሜት እንዳይሰማቸው ማድረግ፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ማጠናከር፣ ምቹ፣ ሰላማዊና የተረጋጋ የመማር ማስተማርና የምርምር አካባቢን የመፍጠር አላማን ይዞ መጀመሩን የጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ ጽ/ቤት አስተባባሪ ዶ/ር ታደሰ ወልደገብርኤል ተናግረዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ "እንደ ሀገር ማህበረ ባህላዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ እሴቶች አሉ" ያሉ ሲሆን፤ "አንድነት፣ ጉርብትና፣ የክርስትና አባትነትና መሰል እሴቶቻችን ከባህል ከአካባቢ፣ ከዘር፣ ከጎሳ ተለይተው የተሳሰርንባቸው ትልቅ ማህበረ ባህላዊ እሴቶቻችን ናቸው" ብለዋል፡፡

"እዚህ ወሳኝ ነባር እሴቶቻችን ዛሬ ድርብርብ ማንነት ላለን፣ ተነጥለን መነጠል ለማንችል፣ ሁላችንም ሁላችንም ውስጥ ሆነን እድንታይ እና አገራችን ያለፉ ዘመናትን ተደጋጋሚ ፈተናዎች እንድታልፍ ያስቻሉ ድንቅ እሴቶች ናቸው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አገር በቀል እውቀት ማለት አገራዊ ማንነትና የሀገር እድገት መሰረት በመሆኑ እነሱን የማጠናከር፣ የመገንባትና እንዲያንሰራራ የማድረግ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
አክለውም "ይህ በጎንደር ዩንቨርስቲ እየተተገበረ ያለው ፕሮጀት ለጠንካራ ሀገራዊ ግንባታ ጥልቅ ትርጉም ያለው፣ የህብረ ብሔራዊነታችንን ቤተሰባዊ መልክ የሚያሳይ እና ነባሩን እሴት በዘመናዊ ተቋም ውስጥ ያንጸባረቀ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ስለሆነም ይህ የጎንደር ዩንቨርስቲ ተሞክሮ በሌሎችም የሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊለመድና በተከታታይ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ