የካቲት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባከናወነው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባው፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሦስት ዓመታት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርትን በመመርመር ለኮሚሽኑ የ1 ዓመት ተጨማሪ የሥራ ዘመን ሰጥቷል።

በምክር ቤቱ የሕግ ጉዳዮች ኮሚቴ የኮሚሽኑን የሥራ ሂደት ከገመገመ በኋላ ባደረገው ምልከታ ኮሚሸኑ አጠቃላይ ሥራውን ማጠናቀቅ እንዲያስችለው የሥራ ዘመኑ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡

በዚህም ሪፖርት ላይ ከፓርላማ አባላት የተለዩዩ ጥያቄዎችንና አስተየቶችን ቀርበው ውይይት ተደርጎበታል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ ዋና ዋና እና አንኳር ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን በማመን ሦስት ዓመቱን የካቲት 14 ቀን በመድፈን የሥራ ዘመኑ ይጠናቀቅ የነበረውን ኮሚሽን ተጨማሪ የአንድ ዓመት ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ወስኗል።

ኮሚሽኑ በቋሚ ኮሚቴው የተሰጠው የአንድ ዓመት ተጨማሪ ጊዜ ውሳኔ፤ ሦስት የተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡

የምክር ቤት አባላቱም ኮሚሽኑ በተሰጠው ተጨማሪ የሥራ ዘመን ተጠባቂ ቀሪ ሥራዎችን እንዲያጠናቅቅ ጠይቀዋል።

የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ 'አዋጅ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማራዘም እንደሚቻል' ይደነግጋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ