የካቲት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የምስረታና ጠቅላላ ጉባዔውን በዛሬው ዕለት ያካሄደው የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር፤ ወይዘሮ በረከት ወርቁን የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አድርጎ መርጧል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ጉባዔ ማህበሩ ሕጋዊ የአሰራር ስርዓት በተከተለ እና የሁሉንም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተወካዮች ባካተተ መልኩ የአዳዲስ የቦርድ አባላትን እና አመራሮችን ምርጫ አካሂዷል።

በምርጫው መሠረት 11 የቦርድ አባላት የተመረጡ ሲሆን፤ ከነዚህ ተመራጮች ውስጥም በተለምዶ 'በረከት ገበሬዋ' በሚል ሥም የሚታወቁት ወይዘሮ በረከት ወርቁ የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡
በተጨማሪም ወ/ሮ ሣራ ሀሠን ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም፤ ትልቅሠው ገዳሙ ደግሞ የማኅበሩ ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት ሆነው በአባላት አብላጫ ድምፅ ተመርጠዋል።
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የላይሠንሲንግ እና ሬጉላቶሪ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ መስከረም ባህሩ ማኅበሩ ከዚህ በፊት ከሕጋዊነት አንፃር ብዙ ክፍተቶች የነበሩበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በነዚህን ክፍተቶች ምክንያቱም ታግዶ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ አያይዘውም እነዚህን ማኅበራት የመደገፍና የማጠናከር ሥራ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከመሆኑ አንፃር ማኅበሩ በአዲስ መልኩ የማቋቋሚያ አዋጅ በሚፈቅደው መሠረት ሁሉንም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አሳታፊ፣ ነፃና ገለልተኛ በሆነና በዲሞክራሲያዎ መንገድ አዳዲስ የቦርድ አባላት ምርጫ ማካሄዱን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶችን የኢኮኖሚ ኃይል መጎልበት ግንባር ቀደም ሀይል ለመሆን፣ ሀገራዊ ዕድገት ውስጥ ያላቸውን ሚና እና ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎን፣ ተወዳዳሪና ሁለንተናዊ የንግድ ምህዳሩን ማጎልበት የሚል ራዕይን በመያዝ በ2002 ዓ.ም የተመሠረተ ማህበር መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ