የካቲት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር የወጡና ፈቃድ ያላቸው እንዲሁም ያለፈቃድ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያንን ከአረብ ሀገራት ወደ ሀገር የመመለስ ሥራ ቢሰራም፤ ድጋሚ በሕገ-ወጥ መንገድ መሰደዳቸው ተግዳሮት እንደሆነበት የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።
በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር በመሰደድ ወደ አረብ ሀገራት ያቀኑ ዜጎች ለእስር፣ ለእንግልት እና ለተለያዩ ችግሮች በመጋለጣቸው በርካቶችን ወደ ሀገር ቤት መመለስ ቢቻልም፤ በገፊ ምክንያቶች ዳግም ለስደት እየተዳረጉ እንደሚገኙ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሕገ-ወጥ ሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍና ክትትል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጄ ተግይበሉ ተናግረዋል።
ሥራ አስፈጻሚው አያይዘውም፤ ተመላሾች ሥራ አለማግኘታቸው በተለይም በክልሎች ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ክፍተት መኖሩ ዳግም ለሕገ-ወጥ ስደት እንዲዳረጉ ምክንያት እየሆነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ "በሁሉም አካባቢዎች በሚባል ደረጃ የሚታዩ አለመግባባቶች፤ ከስደት ተመላሾች ወደየ አካባቢያቸው ለመመለስ ፍቃደኛ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል" ብለዋል፡፡
ይህም በመሆኑ ለሦስት ለአራት ተመላሾቹ የሚመደበው በጀት በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ እንዲውል እያደረገ መሆኑን አክለዋል። "እነዚህ እና መሰል ችግሮች ተቋሙን እየፈተኑት ይገኛሉ" ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ሥራ አስፈጻሚው አያይዘውም ችግሩን ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ቢሰራም ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ጠቁመዋል።
በዋናነት ለስደት ተመላሾች የሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራዎች መሰራት ላይና ግጭቶችን ወደ ሰላም መመለስ ላይ መተኮር ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፉት 6 ወራት ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ወጥተው ሳውዲ አረቢያ፣ የመን፣ ቤሩት እና የመሳሰሉ ሀገራት ውስጥ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መካከል 33 ሺሕ 900 የሚጠጉ ስደተኞች ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸውን ስለማስታወቁ አሐዱ ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ከእነዚህም ተመላሾች መካከል 1 ሺሕ 60 የሚሆኑት ከፍተኛ ልዩ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ በአጠቃላይ በአንድ ዓመት ውስጥ ከተመለሱት 152 ሺሕ 349 ከስደት ተመላሾች መካከል 47 ሰዎች ከፍተኛ የአካል የሆነ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ከአረብ ሀገራት የተመለሱ ዜጎች ዳግም በሕገ-ወጥ መንገድ መሰደዳቸው ፈተና ሆኖብኛል ሲል የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ
