የካቲት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በ2017 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከቀረቡለት 191 የወንጀል ጉዳዮች እና 167 ከፍታብሔር ጋር የተያያዙ የምርመራ ጥያቄዎችን ከፖሊስና ከፍርድ ቤት ተቀብሎ በፎረንሲክ ምርመራ ማጣራቱን አስታውቋል፡፡

ከእነዚህም ከተጣሪ 358 የፎረንሲክ ምርመራዎች ውስጥ 73 በመቶ ሀሰተኛ መሆናቸውን ማረጋገጡን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ፎረንሲክ ምርመራ ካደራጃቸው ዘመናዊ የላብራቶሪ ክፍሎች አንዱ የሰነድ ምርመራ ላብራቶሪ ሲሆን፤ በሰነዶች ላይ የሚፈፀሙ ፊርማዎችን፣ በቲተሮችና በማህተሞች፣ በባንክ ቼኮች፣ በፖስፖርቶች፣ በተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ላይ የተፈፀሙ ድልዝና ስርዞችን፣ በፅሁፎች እና በቁጥሮችን ይመረምራል።

በተጨማም ከውርስ ጋር የተያያዙ ሰነዶችን እና ከቦታ ካርታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በመመርመር ትክክለኛ እና ሀሰተኛ መሆናቸውን እያረጋገጠ የፍትሕ ሥርዓቱን በማገዝ የድርሻውን እያበረከተ እንደሚገኝ የፎረንሲክ ምርመራ ዲፓርትመንት ገልጿል።

በኢትዮጵያ የፀረ-ሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ሥር መንግሥታዊ እንዲሁም ሕዝባዊ ድርጅት ሰነዶችን በማስመሰል በሙሉ ወይም በከፊል የለወጠ፣ ያሻሻለ፣ የቀነሰ፣ የጨመረ ወይም በማጥፋት ወደ ሀሰተኛነት የለወጠ እንደ ወንጀሉ ክብደት እስከ እድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኅብረተሰቡ ማንኛውም ዓይነት ውሎችን ሲዋዋል፣ Online ግብይቶች ሲያደርግና ሲፈርም በአጠቃላይ ከሰነድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሚገባ ማየትና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ