የካቲት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ዳግም ምዝገባ ሳያከናውኑ በመቅረታቸው ተዘግተው የነበሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚጠብቅባቸውን ሰነዶች ያላሟሉበትን ተጨባጭ ምክንያት እና መስተካከል የሚችልበትን ሁኔታ ለመምከር ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር እየተወያዩ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ገልጿል።

በኢትዮጵያ ህልውናቸውን ማረጋገጥ ያልቻሉና ዳግም ምዝገባ ያላደረጉ፤ 1 ሺሕ 700 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መዘጋታቸው መገለጹ ይታወሳል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ "እገዳ የተጣለባቸው ድርጅቶች እጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ወደ ሥራ የሚመለሱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ምን እየተሰራ ነው?" ሲል አሐዱ ጠይቋል።

በጉዳዩ ምላሽ የሰጡት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የጋራ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሁሴን፤ "እገዳው ከተጣለ በኋላ ምንም አይነት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ወደ ሥራ አልተመለሰም" ብለዋል፡፡

Post image

ሆኖም በድርጅቶቹ በኩል የሚቀርቡ ቅሬታዎችን እልባት ለመስጠት በማሰብ ከዚህ ቀደም ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩትን በመለየት ወደ ሥራ እንዲመለሱ ለማስቻል ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አክለውም እገዳው የተጣለባቸው አንዳንድ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች 'እርምጃ እንደሚወሰድ አልሰማንም' የሚሉ ቅሬታዎችን ቢያቀርቡም፤ ውሳኔወ ከመተላለፉ በፊት በቂ ጊዜ የተሰጠ መሆኑን እና መረጃው ተደራሽ ስለመደረጉም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተሻሻለው አዋጅ መሰረት ዳግም ተመዝግበው ሕጋዊ ህልውናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ መሠጠቱ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎም ምዝገባቸውን ያላከናወኑ ድርጅቶች ላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እገዳ የጣለባቸው ሲሆን፤ የእነዚህም የሲቪል ማህበራት የባንክ ሂሳባቸው በመዘጋቱን ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ ለመክፈል መቸገራቸውንና እጣ ፈንታቸው አደጋ ላይ መውደቁን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ