ጥቅምት 8/2018 (አሐዱ ሬዲዮ)ኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ የምትሰጠው የኢንሹራንስ አገልግሎት ሽፋን 0 ነጥብ 04 በመቶ ብቻ እንደሆነ በግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ የገጠር ፋይናንስ ክፍል የቡድን መሪ የሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ጌታቸው መኮንን፤ ከ80 በመቶ በላይ የግብርና መር ኢኮኖሚ ያላት ኢትዮጵያ በአርሶ አደሮቿ ምርት ላይ ለሚደርስ አደጋ የምትሰጠው የመድኅን ሽፋን ከአንድ በመቶ በታች ነው ብለዋል፡፡

Post image

"ኢትዮጵያ ለአርሶ አደሮቿ የምትሰጠው የግብርና መድኅን ሽፋን ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ነው" ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ "በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ 18 የኢንሹንስ ኩባንያዎች መካከል ለአርሶ አደሮች የኢንሹራንስ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ አግኝተው በመስራት ላይ የሚገኙት 4 ብቻ ናቸው" ብለዋል።

ባለፉት 10 ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ አጋር ድርጅቶች የኢንሹራንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለው ከ3 ሺሕ እንደማይበልጡ የመሪ ሥራ አስፈፃሚ አባሉ ለአሐዱ አስታውቀዋል።

የመድኅን ሽፋኑ አነስተኛ የመሆኑ ምክንያቶች፤ የግብርናውን ዘርፍ በፋይናንስ ሊያጠናክር የሚችል ስርዓት አለመኖር እና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በግብርናው ዘርፍ ብድር የመስጠት ፍላጎት ማነስ ዋነኞቹ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ይህንን ታሳቢ በማድረግ የግብርና ሚኒስቴር ችግሩን ለመቅረፍ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ኩባንያዎች ጋር በመቀናጀት፤ የግብርናውን ዘርፍ በፋይናንስ አቅም ለማሳደግ በሚያስችሉ ስምምነቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ተብሏል።

‎#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ