የካቲት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት መሆንዋ በዐለት ላይ እስኪጻፍ ድረስ ጥረታችን ይቀጥላል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ "ሀገራችን ኢትዮጵያም እንደ ኅብረቱ መቀመጫ ሀገር የሚጠበቅባትን አከናውናለች። አቀባበሉ፣ መስተንግዶውና መርሃ ግብሮቹ እንግዶቻችንን ያስደመመ ነበር።" ብለዋል።
"እንግዶቿ የማይረሳ ትውስታ፣ የማያረጅ ትዝታ እንዲኖራቸው አድርጋለች" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፤ በዚህ የተነሣ የቆይታ ጊዜያቸውን ያራዘሙ እንግዶች ብዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አክለውም፤ "ኢትዮጵያ ለኅብረቱ ዓላማዎች እና መርሖች መሳካት ያላትን ቁርጠኝነት በጉባኤው ዝግጅትና መስተንግዶ በተግባር አሳይታለች" ብለዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ብዙዎች የሚቻላቸውን ሁሉ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በዚህም አዘጋጅ ኮሚቴው፣ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማቶች፣ የፕሮቶኮል ባለሞያዎች፣ የቴሌና የመብራት ተቋማት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የጸጥታ ተቋማት፣ የትራፊክ ፖሊሶች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ሚዲያዎች፣ የኪነ ጥበብና የሰርከስ አባላት፣ ሆቴሎች፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር የሥራ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች፣ የጽዳት ባለሞያዎች፣ እንደ አንድ ልብ ሰሚ፣ እንደ አንድ አካል ፈጻሚ ሆነው መስራታቸውን ተናግረዋል።
"የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ለእንግዶቹ ተገቢውን ክብርና መስተንግዶ በመስጠት፣ መንገዶች ሲዘጉ በትዕግሥት በመጠባበቅ፣ ለጉባኤው ስኬት የሚጠበቅበትን ሁሉ አድርጓል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ለሁላችሁም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በራሴ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ" ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አክለውም "ሁላችንም በሀገር ፍቅር ስሜት በሥርዓት እና በዲሲፕሊን በመሥራታችን እንግዶቻችንን አስደምመናል። የሀገራችንን ከፍታ አሳይተናል" ብለዋል።
"ከአንድ ሺሕ በላይ የሚሆኑት የሚዲያ ሰዎች መልካም ገጽታችንን ለዓለም አሳይተዋል። ከ10 ሺዎች የሚልቁት እንግዶች እየበለጸገች ስለምትገኘው ሀገራችን ምስክሮች ሆነዋል" ሲሉም ገልጸዋል።
"ይህ ትብብራችንና ለሀገራችን ስኬት ያለን ቁርጠኝነት፣ ከጉባኤው በኋላም እንደሚቀጥል አምናለሁ።" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ "ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት መሆንዋ በዐለት ላይ እስኪጻፍ ድረስ ጥረታችን ይቀጥላል" ሲሉ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ