የካቲት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በያዝነው ዓመት ኢትዮጵያ የቢዝነስ ቱሪዝምን በመጠቀም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎችን በመቀበል ታስተናግዳለች ተብሎ እንደሚጠበቅ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው እንደሚሆን ነው የተገለጸው፡፡
እስካሁን ድረስ ባለው አሰራር መሰረት ምን ያክል ቱሪስት ወደሀገር ውስጥ ገባ? ምን ያክሉስ የሀገር ውስጥና የውጪ ነው? እንዲሁም ምን ያክል ቀን አሳለፈ? የሚሉትን መረጃዎች ለማወቅ ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በሚያገኘው ዳታ ተመስርቶ እንደሚሰራ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ጌትነት ይግዛው ለአሐዱ ገልጸዋል።
"በመሆኑም በ2016 በጀት ዓመት በተመረቀው የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት አማካኝነት፤ በዚህ ዓመት የነበሩ ክፍተቶችን በመሙላት እና የቱሪስትን ሙሉ መረጃ በማጠናቀር በቅርብ ጊዜ ከ1 ሚሊዮን በላይ ቱሪስት እናስተናግዳለን" ሲሉ ተናግረዋል።
ዘመናዊ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ከ60 ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም ይህንን ያህል ቁጥር ያለው የውጭ ሀገር ጎብኚ እንዳላስተናገደ የገለጹት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ የያዝነው ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ለዚህም እንደዋና ምክንያት ያነሱት ሀገሪቱ አንድ ትልቅ የቱሪስት ቡድን ተብሎ ከ21 እስከ 25 ሰው ከሚሳተፍበት የባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቱሪዝም ይልቅ፤ በአንድ ጊዜ ከ1 ሺሕ 500 እስከ 2000 የጉባዔ ተሳታፊዎችን በሚያካትተው ወደ "ቢዝነስና ሌዠሪ ቱሪዝም ዘርፍ መሸጋገሯ እንደሆነ አስታውቀዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ53 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች መከናወናቸውን በመጥቀስ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ 22 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እያንዳንዳቸው በፈረንጆቹ 2025 እስከ 2027 ዓ.ም. በትንሹ 6 ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን እንደሚያካሂዱ ገልጸዋል።
በአጠቃላይም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ300 እስከ 400 የሚጠጋ የዓለም አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ ይስተናገዳል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።
አዲስ አበባ ለቢዝነስ ቱሪዝም እንደዋና መናኸሪያ ትሁን እንጂ፤ በቀጣይ የክልል ዋና ዋና ከተሞችን በማነቃቃት ወደ ቢዝነስ ቱሪዝም እንዲመጡ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መሪ ሥራ አስፈፃሚው ለአሐዱ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ኢትዮጵያ በቢዝነስ ቱሪዝም ከ1 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎችን ታስተናግዳለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለጸ
