ጥር 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ተቋማት ሲጠቀሙበት የቆዩት የገቢ ደረሰኝ እስከ የካቲት 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ብቻ እንደሚያገለግልና ከየካቲት 3 ጀምሮ ገቢዎች ሚኒስቴር በሚያሳትመው አዲስ ደረሰኝ ግብይት መካሄድ እንደሚጀምር መገለጹ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት ከየካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገውን ልዩ መለያ (QR ኮድ) የተካተተበት ደረሰኝ ለማሳተም ሁሉም ክልሎች ከታሕሳስ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በፊት መረጃዎቻቸውን አሟልተው መላክ እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል።

ይሁን እንጂ እስከአሁን ይህን መመሪያ ተግባራዊ ያደረጉት አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ እና ሌሎች 6 ክልሎች ብቻ መሆናቸውን፤ በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ መረጃና የሽያጭ መመዝገቢያ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ ዚነት አበጋዝ ለአሐዱ ተናግረዋል።

አክለውም፤ ግብር ከፋዮቹ አስፈላጊዎቹን መረጃዎች በተመደበው ጊዜ አለመስጠታቸው የደረሰኙ የህትመት ጥራት ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር፣ እንዲሁም ማተሚያ ቤቱ ላይ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል አስረድተዋል።

ክልሎች እስከ ጥር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ በተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ መረጃዎቻቸውን እንዲያስገቡ ያሳሰቡት ዚነት አበጋዝ፤ በቀሩት ጥቂት ቀናት መረጃዎቻቸውን የማያስገቡ እና የማይመዘገቡ ግብር ከፋዮች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

አዲሱ QR ኮድ የተካተተበት ደረሰኝ ከየካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ እንደሚውል እና የቀድሞው ደረሰኝ እስከ የካቲት 2 ብቻ እንደሚያገለግል ከዚህ ቀደም አሐዱ መዘገቡ የሚታወስ ነው።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ