የካቲት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፋር ክልል በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የተፈናቀሉ ቤተሰቦችን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስም ሆነ የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን ለመጠገን እንዳልተቻለ እና አካባቢው ላይ አሁንም የመሬት መንቀጥቀጥ እየተከሰተ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሳ አደም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

በመሬት መንቀጥቀጡ 250 የሚሆኑ መምህራን ከሥራቸው ተፈናቅለዋል ያሉት ኃላፊው፤ ከአምስት ሺሕ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

አካባቢው ላይ የነበሩትን ነዋሪዎች በማንሳት ወደ ሌላ አካባቢ መዛወራቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ባሉበት መጠለያ አካባቢ 20 የሚደርሱ ጊዜያዊ የመማሪያ ማዕከላትን በማቋቋም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡

ነገር ግን ወላጆች እና ልጆች ላይ ባለው ፍርሃት ምክንያት ወደ ትምህርት ገበታቸው ተማሪዎችን የሚልኩ ወላጆች እና የሚመጡ ተማሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አደጋው በአካባቢው ላይ አሁንም መቀጠሉን ያነሱት የትምህርት ቢሮ ኃላፊው፤ እስካሁን ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች 37 መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በነበረው ሁኔታ የተፈጠረባቸውን የሥነ-ልቦና ጫና ለመቀነስ ያግዛል በሚል የሥነ ልቦና ድጋፍ ስልጠናዎችን ለመስጠትም እየተሞከረ መሆኑን አቶ ሙሳ ተናግረዋል፡፡

በአፋር ክልል ከ2017 መባቻ ጀምሮ በተደጋጋሚ በሚከሰተው ርዕደ መሬት ምክንያት ከክልሉ ገቢ ረሱ ዞን በዱለሳ እና በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳዎች "ለአደጋው ተጋላጭ ናቸው" ተብለው የተነሱ ከ54 ሺሕ በላይ ዜጎች በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው መገለጹ ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ