መጋቢት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት የ8 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት ለማስመዝብ እየሰራች መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚህም ከምክር ቤቱ አባላት የኢኮኖሚውን ዘርፍ በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ "ባለፉት ስምንት ወራት በዋና ዋና የኢኮኖሚ አመላካቾች ታላላቅ ስኬቶች ተመዝግበዋል" ብለዋል።
ሀገሪቱ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ በመዘጋጀት እየሰራች እንደምትገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መሪ ዕቅዱ መነሻ ያደረገ የ5 ዓመት እና የ1 ዓመት የተግባር ዕቅድ ተዘጋጅቶ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
አክለውም የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ተቋማት ያለፈው ዓመት የሰብሰሃራን የኢኮኖሚክ እድገት አራት ነጥብ ሁለት በመቶ እንደሚሆን መገመታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮች ቢያጋጥሙም ሀገሪቱ፤ 8 ነጥብ 1 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን ተናግረዋል፡፡
"በዚህ ዓመት ለሰብ ሰሃራን ኢኮኖሚያዊ እድገት የተሰጠው ግምት ብዙም የራቀ ባይሆንም፤ ኢትዮጵያ 8 ነጥብ 4 በመቶ ለማደግ አቅዳ እየሰራች ትገኛለች" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማብራሪያቸው "ኢትዮጵያ ዛሬ በአፍሪካ ከፍተኛው ስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች" ብለዋል፡፡
ይህንንም ሲያብራሩ በዚህ ዓመት ከሰባት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር ያለነሰ መሬት በሰንዴ ሰብል መሸፈኑን የገለጹ ሲሆን፤ ከ300 ሚሊዮን ኩንታል ያላነሰ ምርት እንደሚጠበቅ ለምክር ቤቱ አስታውቀዋል፡፡
አክለውም፤ "ኢትዮጵያ ዛሬ በአፍሪካ ከፍተኛው ስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች። በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያማቸው ሰዎች ቢኖሩም እውነታው ይህ ነውና ማመን አለባቸው" ሲሉ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በበጀት ዓመቱ የ8 ነጠብ 4 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛው ስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች" ብለዋል
