የካቲት 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከዚህ ቀደም በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚታወቁት አካባቢዎች ላይ ቁጥጥር በመጠናከሩ፣ በአካባቢዎቹ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት እእዲሁም የአዘዋዋሪዎቹ መተላለፊያዎች በመታወቃቸው፤ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ድንበር የሚያሻግሩ አዘዋዋሪዎች የምስራቁን የኢትዮጵያ ክፍል እየመረጡ መሆኑን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁ ወንጀሎችና ድምበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ኢዮሲያስ አበጀ፤ በሐረሪ እና በድሬዳዋ በኩል ወደ ጅቡቲ እንዲሁም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚሻገሩ ሰዎች ቁጥር ከየትኛውም ጊዜ በላይ እያሻቀበ እንደሚገኝ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚደረገው ፍልሰትና በስሜን ምዕራብ በሑመራ በኩል የሚካሄደው ፍልሰት እየጨመረ መምጣቱንም ነው የተናገሩት፡፡

ሥራ አጥነትና በደላሎች መታለል ለሕገ-ወጥ ፍልሰቱ ገፊ ምክንያት እንደሆኑ ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ "የባህር ላይ ወጀብ አይኖርም ተብሎ በሚገመትባቸው ወቅቶች የሕገ-ወጥ ፍልሰተኞቹ ቁጥር በከፍተኛ መጠን ይጨምራል" ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አያይዘውም ሕገ-ወጥ ፍልሰተኞቹ ከሚነሱባቸው አካባቢዎች እስከ መዳረሻ ሀገራት ድረስ በተዘረጋ መዋቅር እና ቅንጅታዊ አሠራሮች ፍልሰቱን ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ