የካቲት 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በማይናማር በሚገኙ የሳይበር ወንጀል ካምፖች በግዳጅ ሠራተኝነት ተይዘው የነበሩ "138 ኢትዮጵያውያን" ተለቅቀው በትናንትናው ዕለት ወደ ታይላንድ መግባታቸውን በሀገሪቱ የሚገኝ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ምንጮችን ጠቅሶ ለቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል።

ኢትዮጵያውያኑ ዜግነታቸውን የማጣራት እና ሌሎች ሂደቶችን ካለፉ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ምንጮቹ ገልጸዋል።

በደቡብ ምሥራቅ እስያዋ ማይናማር ብዛት ያላቸው የሳይበር (የበይነ መረብ) ማጭበርበር የሚከናወንባቸው ካምፖች የሚገኙባት ሀገር ነች።

በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ቢያንስ 154 ግቢዎች ውስጥ የሚፈጸሙት የማጭበርበር ወንጀሎች በአብዛኛው የሚከናወኑት "የሥራ ዕድል ታገኛላችሁ" በሚል ተታልለው በግዳጅ ለዚህ ድርጊት በተዳረጉ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ሲሆን፤ ከእነዚህ ዜጎች መካከልም በርካታ ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል።

የኢትዮጵያውያኑ ተጎጂዎች ወላጆች ኮሚቴ 300 ገደማ ኢትዮጵያውያንን ሥም የመዘገበ ሲሆን፣ አጠቃላይ በተለያዩ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ የሀገሪቱ ዜጎች ቁጥር "ሦስት ሺሕ ይደርሳል" ተብሎ እንደሚገመት ተገልጿል።

Post image

ኢትዮጵያውያኑ መደብደብ እና በኤሌክትሪክ ሾክ መደረግን ጨምሮ የተለያዩ የማሰቃየት ቅጣቶች እንደሚፈጸምባቸው በተደጋጋሚ ሲገለጽ ይሰማል።

ማይናማር በሚገኙ እነዚህ ካምፖች ውስጥ የነበሩ ከ19 ሀገራት ከተወጣጡ 260 ዜጎች ትናንት ረቡዕ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሰዓት ተለቅቀው አጎራባች ወደ ሆነችው ታይላንድ መግባታቸውም ነው የተገለጸው።

ከምንጮች የተገኘው የታይላንድ መንግሥት የውጭ ሀገራት ዜጎች ዝርዝር መረጃ እንደሚያሳየው፤ ከ260ዎቹ ተመላሾች መካከል "138 ያህሉ ኢትዮጵያውያን" ናቸው።

አንድ ምንጭ፤ "በዚህ ቡድን ውስጥ ብቻ 138 ኢትዮጵያውያን አሉ። ነገር ግን ማንነታቸው ላይ የፓስፖርት እና ሌሎች መረጃዎች አልተሰበሰቡም" ብለዋል።

ከኢትዮጵያውያን ቀጥሎ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የጎረቤት ሀገር ኬንያ ዜጎች ሲሆኑ፣ 24 ኬንያውያን ተለቅቀዋል ተብሏል።

የፊሊፒንስ ዜጎች በ16፤የማሌዥያ ዜጎች ደግሞ በ15 ተከታዮቹን ደረጃዎች እንደያዙ ከምንጮች የተገኘው የታይላንድ መንግሥት መረጃ አመላክቷል።

ከተለቀቁት ሰዎች መካከል የኡጋንዳ፣ የታንዛኒያ፣ የናይጄሪያ እና የቡሩንዲ ዜጎች እንደሚገኙበት ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።

በተጨማሪም ከተለቀቁት ዜጎች መካከል 221 ያህሉ ወንዶች፤39 የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች እንደሆኑም ተጠቅሷል።

ከተለቀቁት የተለያዩ ሀገራት ዜጎች መካከል "የተወሰኑት ታይ ቻንግ" ከተባለው የማጭበርበሪያ ካምፕ እንደሆነ ቀሪዎቹ ደግሞ "ኬኬ ፓርክ" እና "ሽዌ ኮኮ" ከተባሉት ብዛት ያላቸው ካምፖች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች ነው ተብሏል።

በካምፖቹ ውስጥ የነበሩት 260 ሰዎች እንዲለቀቁ ያደረገው አካባቢውን የሚቆጣጠረው "ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ" የተባለው ታጣቂ ቡድን ስለመሆኑ ተነግሯል።

ቡድኑ፤ በካምፑ የነበሩ ሰዎችን ያስለቀቀው አጎራባቿ ታይላንድ ካምፖቹ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ በሚል፤ ወደ አካባቢው የሚሄደውን የኤሌክትሪክ ኃይል እና የነዳጅ አቅርቦት ካቋረጠች በኋላ መሆኑም ተመላክቷል።

ካረን በተባለው የማይናማር ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድኑ ያስለቀቃቸውን ሰዎች ወደ ታይላንድ የላከ ሲሆን፤ ሲደርሱም የሀገሪቱ ሠራዊት ተረክቧቸዋል።

የተለቀቁት ሰዎች በአሁኑ ሰዓት በታይላንድ መንግሥት መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙም ተነግሯል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ