የካቲት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በመንግሥት በኩል በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ ሕጎች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እና አካባቢዎች ላይ ተግባራዊ መደረግ አለባቸው ሲል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሳስቧል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይህንን የገለጸው ባለፉት ሦስት ዓመታት በትግራይ ክልል የምክክር ሥራ በተመለከተ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለመጀመሩን ተከትሎ ነው፡፡

ኮሚሽኑ በአማራ ክልል በአራት ክላስተር በመክፈል በደሴ፣ ባህርዳር፣ ሰሜ ሸዋ እና ጎንደር ከተሞች የተሳታፊ ልየታ መጀመመሩን የገለጸ ሲሆን፤ በትግራይ ክልል ግን ምንም ዓይነት ሥራ መስራት አለመቻሉን አስታውቋል፡፡

ይህንን በሚመከለከት የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያር እንደተናገሩት፤ "የትግራይ ክልል አንዱ የፌደራል ግዛት መሆኑ መታወቅ አለበት" ብለዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ የሚወጡ ማንኛውም ሕጎች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች መተግበር ያለባቸው በመሆኑ፤ የፌደራል መንግሥቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት መንግሥት የትግራይ ክልል ወደ ምክክር እንዲመጣ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት በማንሳት፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩም ወደ ምክክር ለመምጣት ቁርጠኛ መሆን እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

ኮሚሽነር መላኩ አክለውም፤ "አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ይህንን ሂደት ይፈልገዋል "ያሉ ሲሆን፤ ወደ ምክክር ለማምጣት በቁርጠኝነት መሰራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

"ከግጭት የሚያተርፍ ማንም የለም" የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ "ሁሉም የኅረተሰብ ክፍል ለሰላም ሚናውን ሊወጣ ይገባል" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቀሪው አንድ ዓመት ግዜ ውስጥ በአማራ እና ትግራይ ክልል ቀሪ ሥራዎችን ለመስራት እቅድ መያዙን መናገሩ ይታወሳል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ 'የትግራይ ሕዝብ ተወካይ በምክር ቤት ባለመኖሩ እና የአዋጁ መፅደቅ የወከለው በሌለበት ኮሚሽኑ ላይ እንዴት ሊስማማ ይችላል?' የሚል የብዙኃኑ ጥያቄ ከተለያየ አቅጣጫ ሲነሳ ተሰምቷል፡፡

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በበኩላቸው፤ "የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ብቻ ሳይሆን በርካታ አዋጆችን ያጸድቃል" ብለዋል፡፡

ትግራይ በጦርነት ውስጥ በነበረበት ወቅትም በርካታ አዋጆች መውጣታቸውን ያስታወሱ ሲሆን፤ "ከእነዚህ መካከል የኮሚሽኑ አዋጅ ይገኝበታል" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

"ይሁን እንጂ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳር በዛን ወቅት የወጡ አዋጆችን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ጨምሮ የሚቀበሉት መሆኑን አረጋግጠውልናል" ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም "የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢትዮጵያን የሚወክል በመሆኑ፤ ምክክሩ በመላው ሀገሪቱ የሚተገበር ጉዳይ መሆኑ መታወቅ አለበት" ብለዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ