የካቲት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የተሳታፊ ልየታ እና አስተባባሪ ስልጠና መስጠቱን ከዚህ ቀደም ሲገልፅ የቆየ ቢሆንም የአጀንዳ ልየታ ሥራዉ መቼ እንሚጀምር አላስታወቀም።
ኮሚሾኑ በዛሬዉ ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው የጋዜጣዊ መግለጫ፤ የሦስት ዓመቱ የኮሚሽኑ ቆይታ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥቷል።
ሦስት ዓመቱ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም የሞላው ኮሚሽኑ፤ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት በተወካዮች ምክር ቤት የቆይታ ግዜው ለአንድ ዓመት እንዲራዘምለት ተደርጓል።
ኮሚሽኑም በዛሬው የሶስት ዓመት የሥራ አፈፃፀሙን ባቀረረበት መድረክ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር መሀሙድ ድሪር፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የተሳታፊ ልየታ እና የአስተባባሪ ስልጠና መስጠቱን ገልጸዋል።
በዚህም ኮሚሽኑ ተሳታፊዎች ልየታ ሲባል በባህርዳር፣ ደሴ፣ ጎንደር እና ሰሜን ሸዋ አራት ክላስተሮች ላይ ሥራዎችን መጀመሩን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በትግራይ ክልል የክልሉን ፍቃደኝነት እና ትብብር የሚያሳይ ከሆነ ሥራዎችን መጀመር እንደሚቻል ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የኮሚሽኑን የሦስት ዓመት የሥራ አፈፃጸም ያቀረቡ ሲሆን፤ "ምክክር ለኢትዮጵያ አዲስ ነው" ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ጦርነት፣ ግጭት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ኮሚሽኑን ያጋጠመው ችግር መሆኑን የገለጹት ዋና ኮሚሸሩ፤ "የፖለቲካ ፖርቲዎች ተሞልተዉ አለመሳተፍ፣ የታጠቁ ሃይሎች ወደ ምክክር አለመምጣት ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ይገኙበታል" ብለዋል።
ኮሚሽኑ በአንድ ዓመት ግዜ ውስጥ የአማራ ክልል እና የትግራይ ክልልን የአጀንዳ ማሰባሰብ ጨምሮ ዋናውን ጉባኤ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል 4 ከተሞች የተሳታፊ ልየታ ማካሄዱን አስታወቀ
