"በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚቻለዉ ሕዝቡም ከስቃይ መዳን የሚችለዉ ኤርትራ ጧሯን ከኢትዮጵያ ማስወጣት ስትችል ነው" ሲሉ የተናገሩት፤ የኢሮብ አኒና ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ተስፋዬ አዉዓላ ናቸዉ።

"ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የፌደራል መንግሥት ኤርትራ ጧሯን ከኢትዮጵያ ግዛት ለቃ እንድትወጣ ይፋዊ የሆነ ጥሪ ማድረግ ሲችል ነው" ብለዋል፡፡

የድንበር ኮሚሽን ውሳኔንም በተመለከተ በሁለቱ ሀገራት መንግሥታት እንዲሁም በድንበር አካባቢ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች በውይይት መፍታት እንዳለባቸውም አቶ ተስፋዬ አሳስበዋል።

"ነገር ግን ማንኛዉም ዉይይት ከመደረጉ ቀድሞ የኤርትራ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ግዛት መዉጣት አለበት" ሲሉ አክለዋል።

"ከሰሜኑ ጦርነት ወዲህ የኤርትራ ሰራዊት ግማሽ ወረዳ ያህሉን የኢሮብ አካባቢን ጨምሮ ይዞ ይገኛል። በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት የድንበር አካላይ ኮሚሽን በአየር ላይ ማስመሩ አሳውቆ ነበር" የሚሉት ደግሞ የቀድሞው ዲፕሎማት ዳያሞ ዳሌ ናቸዉ።

"ይህንን ለብዙ ጊዜ ሲንከባለል የመጣዉን ችግር መፍታት ወሳኝ ነው" ያሉት የቀድሞ ዲፕሎማቱ፤ "መሬት ላይ ድንበር ማካለል ባልተደረገበት የራስ አድርጎ መዉሰድ ተገቢ አይደለም" ብለዋል፡፡

የኤርትራ ሠራዊት 6ዐ በመቶ የሚሆነዉን የኢሮብ ማህበረሰብ መቆጣጠሩን የኢሮብ አኒና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ለአሐዱ ገልጿል።