ጥር 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቅርብ ቀናት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ ፍሰትና አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም ታላላቅ ፕሮግራሞችን ቁጥጥር ማድረግ የሚችሉ የድሮኖች ስምሪት እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ተናግረዋል፡፡
የፀጥታ ጥምር ኃይል በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ያለውን የፀጥታ ሁኔታን በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ግምገማውን የመሩት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የወንጀል መከላከል ሥራችንን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ የሚችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም "በቅርብ ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ ፍሰትና አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም ታላላቅ ፕሮግራሞችን ቁጥጥር ማድረግ የሚችሉ የድሮኖች ስምሪት ይደረጋል" ብለዋል፡፡
አያይዘውም "ከዛሬ 15 ቀን በፊት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የከተማችን ሰላምና ደህንነት ዘላቂ እንዲሆን የፀጥታ ጥምር ኃይሉ ተቀናጅቶ በመሥራቱ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል፡፡" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዚህም አሁን ላይ በአዲስ አበባ ምቹ የፀጥታ ሁኔታ ያለበትና በቀጣይ በኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል እና የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በሰላም እንዲጠናቀቁ ከወዲሁ ይህንን የሚመጥን ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ አልፎ አልፎ የሚገጥሙ የተሽከርካሪ ዕቃዎችና የሞባይል ስርቆቶች የሚስተዋሉ ስለሆነ፤ ሕዝቡ እና ቱሪስቶች ያለ ስጋት በነፃነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ ችግሮቹን ለማስወገድ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ በከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰራም መናገራቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡