ታሕሳስ 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የትጥቅ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ውስጥ ያሉ ሕጻናትን ለመጠበቅ የሚያስችል ውሳኔ በቅርቡ አጽድቋል፡፡

የጸጥታው ምክር ቤት በግጭት አካባቢ የሚኖሩ ሕጻናት ግድያ እና እገታ ስጋት ውስጥ መግባቱን ተከትሎ፤ ጉዳቱን ለመከላከል ያስችላል ያለውን ውሳኔ ነው በሙሉ ድምጽ ያሳለፈው፡፡

ከ100 በሚበልጡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገራት ትብብር የተዘጋጀው የውሳኔ ሃሳብ፤ "ሕጻናትን በትጥቅ ግጭቶች ውስጥ መመልመል እና መጠቀም ሁሉንም የዓለም አቀፍ ሕጎች የሚጥስ ነው" ሲል አውግዟል፡፡

ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በትጥቅ ግጭቶች ሊጎዱ የሚችሉ ሕጻናትን ከመጠበቅ ጋር የተያያዙ ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን እንዲያከብሩ አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ሙሉ ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የውሳኔ ሃሳቡ ሁሉም አባል ሀገራት እና የተባበሩት መንግሥታት ግጭቶችን በሚመለከቱ ሁሉም ተዛማጅ ተግባራት ውስጥ የሕጻናት ጥበቃን እንዲያካትቱ ጠይቋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት እና የጦር ግጭቶች (ሲ.ኤሲ.ኤሲ) ዋና ፀሀፊ ልዩ ተወካይ ቨርጂኒያ ጋምባ፤ "የፀጥታው ምክር ቤት በሕጻናት ጥበቃ ለማድረግ ያሳለፈውን ረቂቅ ውሳኔ በደስታ ተቀብየዋልሁ" ብለዋል፡፡

የውሳኔ ሃሳቡ፣ 14ኛው የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ በልጆች እና በትጥቅ ግጭቶች ላይ ያተኮረ፣ በግጭት እና ከግጭት በኋላ ባሉ አካባቢዎች ዘላቂ የሕጻናት ጥበቃ አቅሞች አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት ይሰጣል፡፡

ይህም "የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ሥራዎች ሽግግር እየጨመረ በሄደበት ወቅት፤ ጠቃሚ መልዕክት ያስተላልፋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል" ነው የተባለው።

"የፀጥታው ምክር ቤት አባላት በትጥቅ ግጭት ለተጎዱ ሕጻናት ለሚያደርጉት ተሳትፎ እና ድጋፍ ቨርጂኒያ ጋምባ ምስጋና አቀርበዋል፡፡

"በግጭት የሚጎዱ ሕጻናት እጅግ ፈታኝ የሆነበት ዓመት እንደሚያበቃ ተስፋ የተጣለበት ውሳኔ ነው" ያሉት ዋና ፀሀፊዋ፤ "የሕጻናትን ፍላጎቶች በተሻለ እና በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት አስፈላጊ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡