ታሕሳስ 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ላይ ትንባሆ እንዳይጨስ በአዋጅ የተደነገገ ሕግ የወጣለት ቢሆንም፤ በአንዳንድ ተቋማት ላይ ግን ሕጉ እየተተገበረ አለመሆኑ ተነግሯል፡፡
የትንባሆ ጭስ ከአጫሹ በተጨማሪ በአከባቢው በሚገኙ በሌሎች ሰዎች ላይ የሚያደርሰውን የጤና ጉዳት ለመታደግ እየተሰራ እንደሚገኝ፤ የአዲስ አበባ ምግብ እና መድሃኒት ባስልጠን የኮሚኒኬሽን ዳይሪክተር ወ/ሮ ወርቅነሽ ፍቄ ተናግረዋል፡፡
በጤና ተቋማት ላይ በትምህርት ቤቶች እንዲሁም ህብረተሰቡ በጋራ በሚጠቀምባቸው ቦታዎች ላይ ትንባሆን ማስጨስ እንደማይቻል የተገለጸ ሲሆን፤ ሙሉ ለሙሉ ትንባሆን ማስጨስ የሚከለክሉ ተቋማት ቢኖሩም በአንዳንድ ተቋማት እና ቦታዎች ላይ ግን አሁንም አለመተግበሩ ተነግሯል፡፡
ከዚህ ቀደም ትንባሆ ማስጨሻ ስፍራ ተፈቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ በአሁኑ ሰዓት ትንባሆ ማስጨስ እንደማይቻል የተናሩት ዳይሬክተሯ ህብረተሰቡም ትንባሆ እንዳይጨስ ሊጠይቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም ትንባሆን በፍሬ መሸጥ እንደማይቻል አስታውሰው፤ በትንባሆ ማሸጊያው ላይ ያሉ ትዕዛዞችን መተግበር እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡
ዳይሬክተሯ አክለውም ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ የተከለከሉ የትንባሆ ምርቶች ላይ የክትትል ሥራ እንደሚሰራ እና ሕዝብ በተሰበሰበበት አካባቢ ትንባሆን በሚያስጭሱ ተቋማት ላይ እርምጃ የሚወሰድበት አሰራር ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም የጤና ድርጅት የወጣውን የትንባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን ተቀብላ ያፀደቀች ቢሆንም፤ የመቆጣጠር ሥራ እና የሕጉ ተፈፃሚነትን መከታተል ላይ ግን በርካታ ክፍተቶች መኖራቸው ተገልጿል፡፡
የአለም ጤና ድርጅት በቅርብ ጊዜ ባወጣው መረጃ መሰረት በአለም አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 25 ቢሊየን ወጣት የትምባሆ ተጠቃሚዎች ይገኛሉ፡፡
በመረጃውም እ.ኤ.አ. በ2022 በዓለም አቀፍ ደረጃ የትምባሆ አጠቃቀም መጠን መቀነሱን ያመላከተ ሲሆን፤ 150 ሀገራት የትምባሆ አጠቃቀምን በተሳካ ሁኔታ እየቀነሱ መሆኑን አስታውቋል፡፡