ጥር 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የእስራኤል ጦር ኃይሎች ቢያንስ 50 ፍልስጤማውያንን በጋዛ ሰርጥ መግደላቸውን የሀገሪቱ የጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ባለሥልጣናቱ በአካባቢው የሚገኙት አል አቅሳ፣ ናስር እና የአውሮፓ ሆስፒታሎች በከባድ የነዳጅ እጥረት ምክንያት በቅርቡ እንደሚዘጉ አስጠንቅቀዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በጋዛ የተኩስ አቁም እና ምርኮኞችን የማስለቀቅ ስምምነት ላይ ተስፋ ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ፤ "ስምምነት ላይ ለመድረስ በጣም ተቃርበናል" ብለዋል።

Post image

በሌላ በኩል የእስራኤል መከላከያ ኃይል እና የእስራኤል የደህንነት ኤጀንሲ የታጋቹን የሱፍ ዚያድኔንን አስከሬን፤ በጋዛ ሰርጥ ራፋህ አካባቢ ከመሬት በታች በሚገኝ ዋሻ ውስጥ አግኝተው ወደ እስራኤል መመለሳቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።

የሱፍ ዚያድኔ በፈረንጆቹ ጥቅምት 7 ላይ ታግቶ የተወሰደ ሲሆን፤ በእገታ ላይ እያለ መገደሉ ነው የተገለጸው፡፡

እስራኤል በጋዛ እየሰነዘረችው ባለው ጥቃት እ.ኤ.አ. ከጥቅምት 7 ቀን 2023 ጀምሮ ቢያንስ 45 ሺሕ 936 ፍልስጤማውያንን ሲገደሉ፤ 109 ሺሕ 274 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተነግሯል። በሌላ በኩል በሃማስ በሚመራው ጥቃት ቢያንስ 1 ሺሕ 139 በእስራኤላዊያን መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከ200 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ተማርከዋል።