የተፈጠረውን እድል ሁሉም የማኅብረተሰብ ክፍሎች ሊጠቀሙበት እንደሚገባም በተደጋጋሚ ተጠይቋል።
ኮሚሽኑ "ማንኛውም 'ሀሳብ አለኝ' የሚል አካል ወደ ውይይት መምጣት አለበት" ብሎ እንደሚያምን የሚገልጹት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ናቸው።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በምክክሩ ለሚሳተፉት የታጠቁ አካላት ኮሚሽኑ ተገቢውን የጥበቃ ዋስትና እንደሚያመቻችና ከኢትዮጵያም ውጪ በፈለጉት ቦታ ውይይት ለማድረግ ፍቃደኛ መሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ "ደጋግመን እንደምንገልጸው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሸን አንዱ ዓላማ ታጥቀው ያሉ ወገኖች ትጥቃቸውን አስቀምጠው ወደ ንግግር እንዲመጡ ማድረግ ነው" ብለዋል። "አሁንም በምዕራብ ኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልል ያሉ ከመንግሥት ጋር በግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ወደ ድርድር እንዲመጡ ጥረት እያደረግን ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ከታጣቂ ሀይሎች ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንደሌለው ገለጸ ሲሆን፤ የመገናኛ ብዙሃን አካላት እገዛ እንዲያደርጉለትም ጥሪውን አቅርቧል።
የቆይታ ግዜው ሊጠናቀቅ ሦስት ወር ያላነሰ ግዜ የቀረው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከታጣቂዎች ጋር በተደጋጋሚ ውይይት ለማድረግ አጀንዳ ለመሰብሰብ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ኮሚሽኑ ከዚህ በተጨማሪም በአማራ፣ በከፊል ኦሮሚያ እና በትግራይ ክልል ሙሉ ለሙሉ የአጀንዳ ስበሰባ ማድረግ አለመቻሉ ይገለጻል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀ ሲሆን፤ ታህሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ሦስተኛ ዓመቱ የሚሞላ በመሆኑ ጊዜው በምክር ቤቱ ካልተራዘመለት ይጠናቀቃል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከታጠቁ ሃይሎች ጋር አሁንም ውይይት ማድረግ እንደሚፈልግ ገለጸ
ሕዳር 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነፍጥ አንግበው ከመንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች ወደ ምክክር መድረኩ እንዲገቡ ጥሪ ሲያደርግ ቆይቷል።