ጥር 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ "ለኢኮኖሚና ፋይናንስ ምህዳራችን ታሪካዊ በሆነ እጥፋት የኢትዮጵያን የመጀመሪያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ደወል ደውልናል" ብለዋል።
አክለውም "ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ባላት፣ ለብልጽግና ሰፊ እምቅ አቅምና ምቹ መንገድ እየተነጠፈላት ባለችው ኢትዮጵያ ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋይዎን ያፍሱ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ሽያጭ፣ ግዥ እና ልውውጥ በቋሚነት የሚደረግበት ሲሆን፤ ለመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የገንዘብ ምንጭ በመሆን ለምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡