የካቲት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የምርጫ ምዝገባና ሥነ-ምግባር አዋጅን እያሻሻለ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ 'ከምርጫ ታዛቢዎች ጋር በተገናኘ አስፋላጊ ሆኖ ሲገኝ የውጭ ታዛቢዎች ይሳተፋሉ' የሚል አንቀፅ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

ይህንን የአንቀፁን ክፍል በተመለከተ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 'መሻሻል ያለበት ጉዳይ ነው' ብለው ሀሳባቸውን የሰጡት፤ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ናቸው፡፡

የኢሕአፓ ተቀዳሚ ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሀይማኖት ከአሐዱ ጋር በነበራቸው ቆይታ "መንግሥት የውጭ ታዛቢዎች ማለትም የአውሮፓ ሕብረት፣ የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የመሳሰሉ ታዛቢዎች እንደ አስፈላጊነቱ ይሳተፋሉ የሚለው አንቀፅ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው" ብለዋል፡፡

"ታዛቢ አስፈላጊ ነው" ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ፤ "በዚህ ረቀቅ ሕግ መሠረት መንግሥት 'ታዛቢ አያስፈልግም' ቢል ታዛቢ እንዳይኖር የሚያደርግ ጭምር ነው" ሲሉ ገልጸውታል፡፡

"የምርጫን ነፃና ፍትሐዊ መሆን ለማረጋገጥ የውጭ ታዛቢዎች ምርጫ ለመታዘብ ፍላጎት እስካሳዩ ድረስ ጥሪ ሊደረግላቸው ይገባል" ያሉም ሲሆን፤ ታዛቢዎች በመንግሥት ግብዣ ብቻ ሳይሆን በራሳቸው ፍላጎት ጭምር ታዛቢ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ሌላው ሀሳባቸውን ለአሐዱ የገለጹት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀመንበር አብርሃም ጌጡ ሲሆኑ ሊቀመንበሩም፤ ከተዛቢዎች ጋር በተገናኘ የተደራጀ ማሻሻያ ለምርጫ ቦርድ ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሊቀመንበሩ 'ታዛቢዎች ማናቸው' የሚለው እና 'እንዴት ነው የሚሰየሙ' የሚለው በግልፅ መቀመጥ እንዳለበት ለቦርዱ መግለጻቸውን ጨምረው ጠቁመዋል፡

የምርጫ ቦርድ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በተለይም ከውጭ ታዛቢዎች በተጨማሪም የተፎካካሪ ፓርቲዎች አንድ ታዛቢ ብቻ ማስቀመጥ እንዳለባቸው የሚያትተው አንቀፅም መሻሻል ያለበት ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲዎቹ ከምርጫ ሥነ-ምግባር ጋር፣ ከፆታ ተሳትፎ ጋር፣ ከመራጮች ዕድሜ ጋር እና ሌሎች በርካታ ማሻሻያዎችን በተመለከተ ማሻሸያ እንዲያደርግ ሲሉ ለቦርዱ ማስገባታቸውን አስታውቀዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ