ታሕሳስ 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በገዢው ብልፅግና ፓርቲ የሚዘወር ንብረት ከሆነ ቆይቷል ሲሉ አሐዱ ያነጋገራቸው የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዋብን) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ገለጹ።
ፓርቲዎቹ 'የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤውን በወቅቱ አላካሄደም' በሚል እና 'በአዲሱ የአመራር ሹመት ዙሪያ የብልፅግና ፖርቲ ተወካይ ያለምርጫ በሥራ አስፈፃሚ ውስጥ ገብቷል' በሚል፤ ከምክር ቤቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እያጤኑት መሆኑን ከሌሎች 3 ፓርቲዎች ጋር በመሆን መግለጻቸው ይታወሳል።
የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ፕሬዝዳንት አማኑኤል ሞጊሳ፤ "በግንቦት ወር ላይ 41 የሚሆኑ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ በወቅቱ እንዲደረግ የሚጠይቅ አቤቱታ ያስገባን ቢሆንም ሰሚ አጥተናል" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
በተደጋጋሚ ይህ የአምስት ፓርቲዎች አቤቱታ ተደርጎ የሚቀርበው ጉዳይ ተገቢ ያለመሆኑንና፤ አቤቱታ ያቀረቡት 41 የሚሆኑ ፓርቲዎች መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
"የጋራ ምክር ቤቱ እንደ ምክር ቤት ለሚወክለው ፓርቲዎች መስራት የሚጠበቅበትን መስራት አለበት" የሚሉት አቶ አማኑኤል፤ "ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ ከተቋም አልፎ የገዢው ፓርቲ ንብረት ሆኗል" ብለዋል።
በዚህም "ምክር ቤቱ ታሪካዊ ስህተት እየሰራ ይገኛል። ለዚህም ማሳያው ማንኛውም አካል በምርጫ መመረጥ ቢጠበቅበትም ብልፅግና ግን ያለ ምርጫ ሥራ አስፈፃሚ አግኝቷል" ሲሉም የምክር ቤቱን ምርጫ ኮንነውታል።
የኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከ50 በላይ የፓለቲካ ፓርቲዎች በሥሩ የያዘ ሲሆን፤ በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ አዳዲስ አመራሮችን መምረጡ ይታወሳል።
ይህንን የምክር ቤቱን ምርጫ ተከትሎ አምስት ከሚሆኑ ፓርቲዎች ብርቱ ተቃውሞ ደርሶበት ነበር። ከእነዚህም ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ይገኝበታል።
የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሙላት ገመቹ በበኩላቸው፤ "ምክር ቤቱ በብልፅግና ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ነው" ሲሉ ሀሳባቸውን ይገልጻሉ።
ለዚህም ሲያስረዱ "በምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት የብልፅግና ፓርቲ በሥራ አስፈፃሚ ውስጥ ቋሚ አባል ተደርጎ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ እንዲገባ መደረጉ ማሳያ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
አሐዱም "ለመሆኑ በጋራ ምክር ቤቱ ውስጥ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ የሌለበት በተቃዋሚዎች ብቻ የሚመራ ምክር ቤት እንዲኖር ነው ወይ ፍላጎታችሁ? ሲል የፓርቲዎቹን አመራሮች ጠይቋል።
የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሙላት ገመቹ ሲመልሱ፤ "ቀደሞውንም መሆን ያለበት እንደሱ ነበር" ያሉ ሲሆን፤ "ሠራተኛ ከአሰሪው ጋር አይደራጅም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
"የጋራ ምክር ቤቱን በተመለከተ ያሉት ችግሮች እስኪፈቱ ውስጥ ሆነን እንዲፈታ እንሞክራለን" የሚሉት ፓርቲዎቹ፤ "ምክር ቤቱን ከመጠለፍ ለማዳን የተቻለንን እናደርጋለን" ሲሉ ገልጸዋል።
ነገር ግን መፍትሄ የሚመጣለት ጉዳይ ካልሆነ ግን፤ ፓርቲያቸው ሌላ አማራጮችን ተመልክቶ መፍትሄ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ይህንን የፓርቲዎች ወቀሳ በመያዝ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ሙከራ፤ ለግዜው ሊሳካ አልቻለም፡፡