ጥር 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትናንትናው ዕለት ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው በንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ላይ፤ 'አራት ተቋማት ማለትም የመንግሥት ተቋማት፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት አይጠየቁም' የሚል ድንጋጌ ተቀምጧል፡፡

የአዋጁ አንቀፅ 4 የሕግ ሰውነት ያላቸው አካላትን በሚመለከት ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ አዋጁ ተፈፃሚ የማይሆንባቸው ተቋማትና ግለሰቦችን ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመሪያ ይወስናል የሚለውን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ጥያቄ አስነስቷል፡፡

አንድ የምክር ቤት አባል ባነሱት ጥያቄም፤ ቋሚ ኮሚቴው በተመሳሳይ በዚህ ጉዳይ ላይ የመንግሥት ተቋማት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት እና ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ላይ ተፈፃሚ እንደማይሆን አዋጁ ማስቀመጡን ያስረዳሉ፡፡

ይሁን እንጂ በተለይም የፖለቲካ ድርጅቶች እና የሀይማኖት ተቋማት ላይ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ሊገኝ የሚችልበት እድል መኖሩን የሚያነሱት አባሉ፤ "ይህ እንዴት ይታያል? በየትኛው ሕግስ ነው የሚዳኙት?" የሚለውን ላይ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

ሀሳባቸውን የተጋሩት ሌላ የምክር ቤት አባል ደግሞ፤ "መንግሥት ኦዲት ስለሚደረግ ችግር አይኖረውም" ይላሉ፡፡ "ነገር ግን ሌሎቹ ሦስቱ ተቋማት ግን አለመጠየቃቸው የሚያሳስብ ነው" ብለዋል፡፡ "በተለይም ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ዶላር ወደ ወጪ በማሸሽ የሚጠረጠሩ በመሆኑ ነፃ መደረጋቸው ተገቢ አይደለም" ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

በትላትናው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛው ዙር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ጉባዔ ተካሂዷል፡፡

በጉባኤው ላይ ተገኝተው የነበሩት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በተለይም በአራቱ ተቋማት ዙሪያ ከምክር ቤት አባላት ጥያቄ እና ማብራሪያ የተጠየቁት ሰብሳቢዋ በምላሻቸውም፤ እነዚህ አራት ተቋማት ከተጠያቂነት ነፃ እንዲሆኑ የወሰነው የኢፌድሪ ፍትህ ሚኒስቴር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላው ከዚህ ጋር ተያይዞ የሀይማኖት ተቋም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ያለ አካል ወንጀል ቢሰራ በመደበኛው ሕግ ተጠያቂ የሚሆንበት መንገድ መኖሩን በአንቀፅ 3 ላይ በግልፅ መቀመጡን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ በንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በሗላ፤ አዋጁ በ4 ድምፀ ተዓቅቦ እና 3 ተቃውሞ በአብላጭ ድምፅ አጽድቋል፡፡