ጥር 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኮሬ ዞን ኬሌ ከተማ በመንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ከ1 ሺሕ በላይ ሠራተኞች፤ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ከመስሪያ ቤታቸው መታገዳቸውን ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው አዲስ የወረዳ አደረጃጀት መተግበሩን ተከትሎ፤ የተወሰኑት ሠራተኞች ከዚህ በፊት በሚሰሩበት ዞን ውስጥ 27 ኪሎ ሜትር ወደሚርቀው እና አዲስ ወደተዋቀረው ወረዳ እንዲሄዱ መታዘዛቸው ተጠቁሟል፡፡
"በዚህም እንዲዛወሩ ከታዘዙት ጥቂት የመንግሥት ሠራተኞች ውጭ ሌሎቻችን ሥራ አጥ እንድንሆን ተደርገናል" ሲሉ ቅሬታቸውን ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ወደ አዲሱ ወረዳ ተዘዋውረው እንዲሰሩ የተደረጉት ሠራተኞችም ቢሆን፤ እንዲዛወሩ የታዘዙት ምንም መሰረተ ልማት ባልተሟላበት ሁኔታ ነው ተብሏል፡፡
አሐዱም የኮሬ ዞን ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቡድን መሪ ጌትነት ገበየሁን ስለ ጉዳዩ ጠይቋል፡፡
ባገኘው ምላሽም "ሠራተኞቹን ከነ አደረጃጀታቸው ወደ አዲሱ ወረዳ እንዲሄዱ እንጂ እንዲቀነሱ አልተደረገም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አክለውም አዲስ ወረዳ ተዋቅሮ አደረጃጀቱ ሲሄድ አዲስ ሠራተኛ ለመቅጠር እንደማይቻል እና የዞን ማዕከልም ከ180 በላይ ሠራተኞችን አወዳድሮ አስቀርቷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
"ሆኖም ሌሎቹን ግን ወደ አዲሱ ወረዳ እንዲሄዱ ከምክር ቤት ትዕዛዝ ስለተላለፈ ቅሬታቸውን መቀበል አልቻልንም" በማለትም ገልጸዋል፡፡
"ፐብሊክ ሰርቪስ የራሱ የሚመራበት አሰራር እንዳለው የሚታወቅ ሲሆን፤ እንዲህ አይነት ውሳኔዎች ከሠራተኛው ጋር ምክክር ሳይደረግ ለምን መተግበር አስፈለገ?" ሲል አሐዱ የዞኑን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ አካላት በቀለን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
እንዲዘዋወሩ ካልታዘዙት ሠራተኞች ውጭ ያሉትና የዞን ማዕከል ላይ ተወዳድረው ለመቅረት የተሳተፉትም፤ "ፈተና የፈተናቸው፣ ውጤት የሚያየው እና ቅሬታ የሚቀበለው አንድ ኮሚቴ በመሆኑ በራሱ የአሰራር ክፍተት ያለበት ነው" ብለዋል፡፡