ጥር 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በራያ ቆቦ ወረዳ የቆቦ ከተማ ኗሪ ወጣት ፈንታው አድሴ የተባለ ግለሰብ እድሜያቸው ከ5 ዓመት እስከ 9 ዓመት የሆኑ ዘጠኝ ህፃናትን አስገድዶ በመድፈር ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጿል፡፡

የቆቦ ከተማ አስተዳደር ፓሊስ የታክቲክ ወንጀል ምርመራ ክፍል ምርመራውን በሰውና በሕክምና ማስረጃ በማጠናከር አጣርቶ ባቀረበው የወንጀል ምርመራ መዝገብ መሰረት፤ የራያ ቆቦ ወረዳ ፍትህ ጽ/ቤት የወንጀል ዐቃቤ-ሕግ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 627(ለ) እና 640(1)(ለ) ድንጋጌዎች መሰረት እድሜያቸው ከ5 ዓመት እስከ 9 ዓመት የሆኑ ዘጠኝ ሕጻናትን አስገድዶ መድፈርና ተደራራቢ ወንጀሎች በሚል ክስ በራያ ቆቦ ወረዳ ፍርድ ቤት ክስ መስርቶ ሲከራከር መቆየቱ ተመላክቷል፡፡

ዐቃቤ-ሕግ እንደ ወንጀሉ ክብደት ተከራክሮ ባስረዳው መሰረት ፍርድ ቤቱ ትናንት ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተከሳሹ በተከሰሰበት 13ቱ ክሶች ጥፉተኛ በመባሉ፤ እሱንም ያርማል ሌሎቹንም ያስተምራል ያለዉን በተከሳሽ ላይ የ25 ዓመት ፅኑ እስራት እና የ10 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ ወስኖበታል።

በፍርድ ሂደቱ አስተያየታቸዉን የሰጡት የተጎጂ ቤተሰቦችም "ውሳኔው ማንኛም ሰዉ ወንጀል ፈፅሞ በመሰወር ከጥፋት ማምለጥ እንደማይችል የተረጋገጠበትና ማንኛዉም ግለሰብ ከወንጀል ድርጊት መታቀብ እንደሚገባዉ የሚያስተምር ፍርድ ነው" ሲሉ መግለጻቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።