ታሕሳስ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሶማሊያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን የኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ ባሰራጨው መረጃ፤ የልዑካን ቡድኑ ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼኽ ማህሙድ ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገዋል።
በተጨማሪም የመከላከያ ሚኒስትሯ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለፕሬዚዳንቱ የተላከ መልዕክትን አድርሰዋል።
![Post image](/_image?href=https%3A%2F%2Fcdn.sanity.io%2Fimages%2Fbede4k7t%2Fproduction%2F57d5aa04002ca25e054d370eb4aaffbd7651be74-720x480.jpg&w=720&h=480&f=webp)
"በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በሶማሊያ እና በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋትን ለማረጋገጥ በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል" ያለው ሚኒስቴሩ፤ "ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የAUSSOM ተልዕኮ ውጤታማ ለማድረግ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል" ሲል ገልጿል።
በቅርቡ የሶማሊያ ከፍተኛ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ጉብኝት በማድረግ ውይይት ለማካሄድ መስማማታቸውም ተመላክቷል።
ይህን ተከትሎም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ዙሪያ ዛሬ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
![Post image](/_image?href=https%3A%2F%2Fcdn.sanity.io%2Fimages%2Fbede4k7t%2Fproduction%2Fb077e4f4d81fa9e65bf93aec65c9749898127b8c-1280x853.jpg&w=1280&h=853&f=webp)
በመግለጫቸውም፤ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት ከአንካራው ስምምነት በኋላ መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር የተመራ ልዑክ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት በማድረግ አልሸባብን በጋራ በመዋጋትና በቀጣናዊ ትብብር ዙሪያ ውጤታማ ውይይት መደረጉን አስታውሰዋል።
በዚህ ሳምንት ደግሞ በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የተመራ ልዑክ በሞቃዲሾ ፍሬያማ ውይይት ማድረጉን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር በሆነችው ጁቡቲ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በጉብኝታቸውም ከጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና ከሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።
በውይይታቸውም አልሸባብን በጋራ መከላከል፣ የነዳጅ መስመር ማስፋፋት፣ ቀጣናዊ ትስስር እና ሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ ውጤቶችን ማስመዝገብ እና የሀገር ገጽታን ማስተዋወቅ የሚያስችሉ ዝግጅቶች እያደረገች መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለዚህም የኢትዮጵያን ገጽታ ማስተዋወቅ የሚያስችሉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሰልጠን እንግዶቿን እየተጠባበቀች መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል በአንካራ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ፤ የሶማሊያ ባለስልጣናት የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ጦር (AUSSOM) ውስጥ የኢትዮጵያ ጦር በድጋሚ እንዲሰማራ ሶማሊያ እንደማትፈልግ የገለጹ ሲሆን፤ ሀገሪቱ በጉዳዩ ላይ እያጤነችበት መሆኑን መግለጻቸውን ይታወሳል፡፡
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው መግለጫው ሁለቱ ሀገራት የጦሩን ተልዕኮ ውጤታማ ለማድረግ በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን ይግለጽ እንጂ፤ በቀጣይ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ጦር ተልዕኮ ላይ የኢትዮጵያ ተሳትፎ እንደሚኖራት የገለጸው ነገር የለም፡፡