የካቲት 4/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ በየጊዜው የልብ ታማሚ ሕጻናት ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፤ በዓመት ወደ ሕክምና የሚመጡ ሕጻናት ቁጥር ከ1 ሺሕ 300 በላይ መሆኑን የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል አስታውቋል፡፡
የማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ህሩይ አሊ በሥራው ላይ የአላቂ መድኃኒቶች እና የሕክምና ግብዓት አቅርቦት ችግር እያጋጠመው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
መድኃኒቶቹ ሀገር ውስጥ የማይገኙ መሆኑን አንስተው፤ ከውጭ ለማስገባት ከ4 ወር በላይ እንደሚፈጅ ገልጸዋል፡፡
"አሁን ባለው ጥናት መሰረት አንድ ታማሚ ሕጻን ለ3 ዓመት ያክል እና ከዛ በላይ ወረፋ እንደሚጠብቅ ያሳያል" ያሉም ሲሆን፤ ይህም መርጃ ማዕከሉ ካቅሙ በታች እየሰራ መሆኑን የሚያመለክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ምክንያት የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ሕሙማን ወረፋቸው ሳይደርስ ሕይወታቸው የሚያልፍበት አጋጣሚ መኖሩንም አንስተዋል፡፡
በሚፈለገው ልክ ለመስራት የመድኃኒትና የባለሙያ እጥረት እንዲሁም ሌሎች ችግሮችንም መፍታት አለመቻሉንም ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ከ7 ሺሕ በላይ የመሆኑ ታካሚዎች ወረፋ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በዓመት ከ600 እስከ 700 ለሚሆኑ ታካሚዎች ብቻ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል በሺዎች ለሚቆጠሩ ሕፃናት የልብ ቀዶ ሕክምና በነፃ የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት የተለያዩ ሥራዎችን የሚሰራ ሲሆን፤ በመጀመሪያዎቹ 20 ዓመታት ውስጥ 2 ሺሕ 600 ታካሚዎችን ወደ ውጭ አገር በመላክ ሕክምና እንዲያገኙ አድርጓል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
አንድ የልብ ሕመምተኛ ሕጻን ሕክምና ለማግኘት ለ3 ዓመት ያህል ወረፋ እንደሚጠብቅ ተገለጸ
