ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግና 3 ሚሊዮን ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የመድህን ሽፋን ለመስጠት አምስት ኩባንያዎች በዛሬው ዕለት የጋራ ስምምነት አድርገዋል።
ይህንን የስምምነት ፊርማ ያኖሩ ኩባንያዎች፤ ኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ አፍሪካ ኢንሹራንስ፣ ኦሮሚያ ኢንሹራንስ፣ ኒያላ ኢንሹራንስና አባይ ኢንሹራንስ ሲሆኑ፤ ፑላ አድቫይዘርስ ለሕብረቱ የቴክኒክ አጋር በመሆን እንደሚሰራ ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ መድን ሰጭዎች ማህበር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳግማዊ ሃይለየሱስ በስምምነቱ ወቅት፤ "የግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት የጀርባ አጥንት ነው ቢባልም ፤በሚፈለገዉ ልክ ትኩረት እየተሰጠበት አይደለም" ብለዋል።
"ይህንን ታሳቢ በማድረግ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍ የሚሰሩ ኩባንያዎች በቅንጅት በመስራት ስኬታማነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል" ሲሉ ዳሬክተሩ አሳስበዋል።
"በኢትዮጵያ የሚገኙ አርሶ አደሮች በተፈጥሮዓዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች እየተጋለጡ ነው" ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ማህበሩ የግብርናው ዘርፍ ለማሳደግ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከፋይናስ ሚኒስቴርና ከሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
በዚህም መሠረት አዲስ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ግብርና መድን ሰጪዎች ጥምረት ከፑላ አማካሪዎች ጋር በመተባበር፤ 3 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን እስከ እ.ኤ.አ 2026 የመድን ሽፋን ለመስጠት ማቀዱን ገልጿል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
አምስት ኩባንያዎች የግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍ በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ
