ጥር 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፋር ክልል አሚባራ አካባቢ ዛሬ ሌሊት 9:20 ገደማ፤ 5 ነጥብ 2 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአሜሪካ ጅኦሎጂካል ሰርቬይ አስታውቋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ ንዝረት በአዲስ አበባ የተለያዩ አካቢዎች መሰማቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህንንም በአዲሱ ገበያ፣ ሽሮ ሜዳ፣ አራት ኪሎ፣ ቀበና፣ ልደታ፣ ጀሞ፣ ፊጋ፣ አያት፣ ጣፎ፣ ኮዬ ፈጬ እንዲሁም በሌሎች የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የአሐዱ ምንጮች አረጋግጠውልናል።
ሌሊት 9 ሰዓት ከ20 አካባቢ የተከሰተው ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ከሰሜን ሸዋ 29 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቀት ላይ የሚገኝ ቦታ ላይ የተከሰተ ሲሆን፤ በተመሳሳይ በዚሁ ሌሊት 8 ሰዓት ከ42 ላይ በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 86 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ በአፋር ገርባ አካባቢ ተከስቷል።
በተጨማሪም ከመተሐራ በ23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፤ በሬክተር ስኬል 4.30 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀ መከሰቱ ታውቋል።
ከሰሞኑ በሬክተር ስኬል እስከ 5 ነጥብ 8 የደረሰ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ በአፋር ክልል መከሰቱ ይታወሳል።
በዚህም የመሬት መንቀጥቀጥ የተነሳ በክልሉ በገቢረሱ ዞን ዱለሳ እና አዋሽ ፈንታሌ ወረዳዎች ከሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች የተፈናቀሉ 54 ሺሕ 180 ኗሪዎችን እንዲሁም ከከሰም ስኳር ፋብሪካ የተፈናቀሉ 4 ሺሕ ሠራተኞችን ጨምሮ ከ58 ሺሕ በላይ ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ ገብተው ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ በክልሉ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አስታውቋል።
ንዝረቱ አዲስ አበባ ድረስ የተሰማ የመሬት መንቀጥቀጥ በአፋር ክልል ተከሰተ
የመሬት መንቀጥቀጡ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 2 ተመዝግቧል